ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይናገራሉ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይናገራሉ (አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ቅጽ 12 ቁጥር 685 የካቲት 23 ቀን 2005 .)

  • እኔ አወዳድሩኝ ብዬ አላውቅም፤ አሁንም ድሮም፡፡
  • ለምርጫው ተብሎ ፓስፖርት አልቀየርኹም፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
  • ደርግን ሳወግዝ የነበሩ ሰዎች እንዴት መንግሥትን ያወግዛል ብለው ፓትርያሪኩን አሳሳቱና አውግዘውኝ ነበር፤ በኋላ ስመጣ በስሕተት ነው ተብሎ አነሡት፡፡
  • ዕርቀ ሰላሙ እንደሚቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ተናግሯል፡፡ በዚያው መሠረት ይቀጥላል፡፡
  • በስብከተ ወንጌል፣ በሃይማኖት አጠባበቅ በኩል የሃይማኖቱን ሥርዐት ያልጠበቁ ሰባኪዎች ጉዳይ በዘፈቀደ እንዳይኾን ለቀድሞው ፓትርያሪክ ያሳስቧቸው ነበር፡፡
  • ቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛውንና ቀጥተኛውን መንገድ እንድትይዝ፣ በውስጧ ያለው ሁሉ መንፈሳዊነትን የተጎናጸፈ እንዲኾን ለመሥራት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ብፁዕነትዎ ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ዕጩ መኾንዎን የሰሙት ከማን ነው?

ሰው ዝም ብሎ ያወራል፡፡ እገሌ ይኾናል ይባላል፡፡ ዕጩ ነኸና ና አሉኝ፤ አሁን ባለፈው የካቲት 13 ቀን ነው አዲስ አበባ የገባኹት፡፡ እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም ከኢየሩሳሌም ተነሥቼ ስገባ፡፡ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ተረቋል ተባለ፡፡ ያ ሕግ ታኅሣሥ 30 ለቅ/ሲኖዶስ ይቀርባልና ና ተባልኹ፤ ሥራ ይበዛ ስለነበር አልተመቸኝም፡፡ ጥር 6 ቀንም ና ተብዬ አልቻልኹም፡፡

ቀደም ሲል የአሜሪካ ዜግነት እንደነበረዎት ሰምቻለኹ፤ አሁንስ?

አዎ፣ በፈረንጅ አቆጣጠር በ1994 – 95 ችግር ነበረብኝ፡፡ የአሜሪካን ፓስፖርት ይዤ ነበር፡፡ አሁን ግን ተለውጧል፡፡ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 2004 ዓ.ም አመለከትኹ፡፡ በግንቦት ወር እንደገና አመልክቼ ተሰጠኝ፡፡ ይኼ ከአሁኑ ምርጫ ጋራ አይያያዝም፡፡ ለምርጫው ተብሎ ፓስፖርት አልቀየርኹም፡፡ በመሠረቱ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ከኾንሁኝ በኋላ ሐሳቤ ወደ ኢትዮጵያዊነቱ ለመለወጥ ነበር፡፡ እንደዚህ ዐይነት ዕጩ እኾናለሁ ብዬ አላሰብኹም፡፡

ግን የአሜሪካ ዜግነት እንዴት ወሰዱ?

አይ÷ እርሱማ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በነርኹበት ጊዜ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ተጽዕኖ ነበረብኝ፡፡ ከተሳላሚዎች ጋራ ደኅንነቶችን እየላኩ ብዙ ችግር አስከትለውብኝ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ተሰደድኩ፡፡ አሜሪካ የነበሩትን ምእመናን ሳገለግል ቆየኹ፡፡ በኋላ ሲኖዶሱ ጠርቶ አጸደቀልኝ፡

በወቅቱ ፓትርያሪክ ተወግዘው ነበር?

መወገዙማ ደርግን አወገዝኹ እኔ፡፡ ደርግን ሳወግዝ የነበሩ ሰዎች እንዴት መንግሥትን ያወግዛል ብለው ፓትርያሪኩን አሳሳቱና አውግዘውኝ ነበር፡፡ በኋላ ስመጣ በስሕተት ነው ተብሎ አነሡት፡፡ የተወገዝኹት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጊዜ ነው፡፡ የተነሣው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም ለቀው አቡነ ያዕቆብ ዐቃቤ መንበር በነበሩ ጊዜ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከመሾማቸው ጥቂት ጊዜ በፊት ነው ይኼ፡፡

ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ተወዳድረው ነበር ይባላል. . . . .

እኔ አወዳድሩኝ ብዬ አላውቅም፤ አሁንም ድሮም፡፡ ብቻ ከየክልሉ ሁለት ሁለት ተወዳዳሪዎች ሲባል ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ እኔ ሳላውቅ ተወዳድሬ እሳቸው ከአምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች ኾኑ፡፡ እኔ ቀረኹ፡፡ ጠርተውኝ የመጣኹት ግን የአቡነ መርቆሬዎስ ምክትል በነበሩት በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ጊዜ ነበር፡፡ መወገዜን እኔም አላውቅም ነበር፡፡ ምን ኾኜ? ስል እንዲህ ተላልፎብኽ ተባልኹኝ፡፡

ብፁዕነትዎ ሲወገዙ ሌላ አቡነ ማትያስ መሾማቸው ትክክል ነበር?

ደኅና፤ በቤተ ክርስቲያናችን ባህል ሁለት ጳጳሳት በአንድ ስም አይጠሩም፡፡ ግን ተደረገ ያን ጊዜ፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ ግፊት አድርገው ነው የተደረገው፡፡ ኾነ ብለው የእኔን ስም ለመውሰድ ያደረጉት ነው፡፡ ስመለስ ጸጸት ውስጥ ገቡ፡፡

ብፁዕነትዎ ፓትርያሪክ ቢኾኑ ዕርቀ ሰላሙ በምን መልክ ይቀጥላል?

ዕርቀ ሰላሙ እንደሚቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ተናግሯል፡፡ በዚያው መሠረት ይቀጥላል፡፡ ከሲኖዶስ የተለየ ሐሳብ ሊኖረኝ አይችልም፡፡

በፓትርያሪክነት ቢሾሙ በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ ለማስመለስ ምን ለመሥራት ዐቅደዋል?

ይህን በሰፊው እንገፋበታለን፡፡ ፓትርያሪክ የመኾን ጉዳይ ሳይኾን እኔም ኾንሁ ሌሎቹ እንዲገፉበት ቅዱስ ሲኖዶሱን እገፋፋለሁ፡፡ ከኾንሁ አለኹ ማለት ነው፡፡ ካልኾንሁ ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሥራዬ ብሎ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ጋራ ተነጋግሮ አንድ መፍትሔ እንዲገኝ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡ ወደ ሌላ ሀ/ስብከት ብቀየርም ይህ ይቀጥላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እርስዎ እንዲመረጡ ይፈልጋል መባሉ ከምን መነጨ?

እኔ ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም ስለዚህ ጉዳይ፡፡

ፓትርያሪክ ቢኾኑ ከአምስተኛው ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ምን የተለየ ሥራ ይሠራሉ?

መቼም እግዚአብሔር የፈቀደውን የምንሠራው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛውንና ቀጥተኛውን መንገድ እንድትይዝ፣ በውስጧ ያለው ሁሉ መንፈሳዊነትን የተጎናጸፈ፣ እውነትኝነትን የተከተለ መኾን አለበት ባይ ነኝ፡፡ እንደ ዓለማዊነት መደረግ የለበትም ባይ ነኝ፡፡ በተቻለ መጠን ይህን ወደ እውነተኛው መንገድ ለመመለስ ተስፋ ነው የማደርገው፡፡

ከአቡነ ጳውሎስ ሥራዎች በጣም የሚያደንቁት?

ቅዱስነታቸው ዓለም አቀፍ ሰው ነበሩ፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዋውቀዋል፡፡ በመንበረ ፓትርያሪክ ግቢ ለጳጳሳት ማረፊያ አሠርተዋል፡፡ ቤት አልነበረም፡፡ መሰብሰቢያ አዳራሽ አልነበረም፡፡ ቤተ መጻሕፍት አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁለቱን አደንቅላቸዋለኹ፡፡

መሻሻል አለበት ብለውስ አቅርበው ያውቃሉ?

አንዳንድ ስሕተቶች ሳይ እነግራቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ÷ በስብከተ ወንጌል፣ በሃይማኖት አጠባበቅ በኩል የሃይማኖቱን ሥርዐት ያልጠበቁ ሰባኪዎች. . .በዘፈቀደ ሲኾን፡፡

ይቀበልዎት ነበር?

ይቀበሉኛል ግን ነገሩ ከባድ ይኾንና የተባለው መቶ በመቶ ላይሠራ ይችላል፡፡ መቻቻል ጥሩ ነገር ይመስለኛል፡፡ መቻቻል ከሌለ ሁከት ነው ያለው፡፡ የሕዝቡንና የሀገርን አንድነት ለመጠበቅ ተቻችሎ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሌላ ምርጫ የለም፡፡ አንዱ የሌላውን ሳይቀማ መኖር መቻል አለበት፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s