በርዕዮት አንገት ላይ፤ የውንጀላ ሰንሰለትና የክብር ሜዳሊያ

በርዕዮት አንገት ላይ

የውንጀላ ሰንሰለትና የክብር ሜዳሊያ

ስለሺ ሐጎስ

ርዕዮት ከታሰረች ጊዜ ጀምሮ በወህኒ ቤት ከምታሳልፈው መከራ ይልቅ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት እስሯን አስመልክቶ በየሚዲያው የሚናገሩት ነገር አጥንትን የሚጠዘትዝ ነበር፡፡ ስለሚጽፉት ነገር አንዴ እንኳ የማያስቡት የአዲስ ዘመን ገጽ 3 አርበኞችና የአይጋ ፎረም የብዕር ስም ፊታውራሪዎች ስለርዕዮት በሚጽፉት ተረት ላይ የሚጠቀሟቸው ስም አጠልሺ ቃላት ለከት አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ርዕዮትን የፕሬስ ነጻነት ምሳሌ አድርገው ሲሸልሟት እነዚህ ምላሶች ወደ ሰገባቸው ይከተታሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ ግን አልሆነም፡፡ ይልቁንም በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ያገኘቻቸውን የክብር ሜዳሊያዎች ለማደብዘዝ ወፋፍራም ሰንሰለታቸውን እየገመዱ በርዕዮት አንገት ላይ ለማጥለቅ ሲንጠራሩ ከርመዋል፡፡ ይህን ሲያደርጉ ኢላማቸው ርዕዮት ብቻ አልነበረችም፡፡ እግረ መንገዳቸው ላይ ያለው እኩይ አላማ በኢትዮጵያ ያሉ ነጻ ጋዜጠኞችን ወኔ መስለብ ነው፡፡

ከሟቹ መለስ ጀምሮ እስከ አቶ በረከት ድረስ ያሉ አንጋፋዎቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እነ ርዕዮት የታሰሩት በጋዜጠኝነት ስራቸው ሳይሆን አሸባሪ በመሆናቸው እንደሆነ ሲናገሩ አስተማማኝ ማስረጃ ያላቸው ይመስል ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ አንዳንድ የቅርብ ሰዎቻችን ሳይቀሩ የሚባለውን ለማመን ሲዳዳቸው በማስተዋሌ በመሪዎቻችን የማስመሰል ብቃት ከመደመም ልተርፍ አልቻልኩም፡፡

አንዳችም ነጻነት በሌለው ፍርድ ቤት የ14 አመት እስራት ከገንዘብ ቅጣት ጋር ተፈርዶባት ሁሉ ነገር ጨለማ በመሰለበት ጊዜ አለምአቀፍ የሴት ጋዜጠኞች ፋውንዴሽን የተባለ ድርጅት አይኖቹን በርዕዮት ላይ አደረገ፡፡ በብዙ ማይል ርቀት ላይ ሆኖ በጥልቅ ጨለማ ውስጥ ያለችውን ንጹህ ሰው ለማየት የንስር አይኖቹን ወረወረ፡፡ “ርዕዮት አሸባሪ ሳትሆን ለአለም ጋዜጠኞች ምሳሌ ናት ስለሆነም በየአመቱ ለጀግና ጋዜጠኞች የምሰጠውን የክብር ሽልማት ሰጥቻታለሁ” ሲል ለአለም ተናገረ፡፡

በዚህ ጊዜ አሸባሪን የሚሸልም አለም አቀፍ ድርጅት አይኖርምና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጥያቄዎች በረከቱ፡፡ ተማሪዎች ሳይቀሩ እንዴት አሉ፡፡ ከወራት በፊት አቶ በረከት ስምኦን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝንት ትምህርት ለሚከታተሉ እጩ “አሸባሪዎች” ልምዳቸውን ሊያካፍሉ በቅጽር ግቢው ተገኝተው ነበር፡፡ በውይይት ክፍለ ጊዜው አንዱ ተማሪ “እናንተ አሸባሪ ብላችሁ ያሰራችኋቸውን ጋዜጠኞች አለም አቀፍ ድርጅቶች እየሸለሟቸው ነው፡፡ ይሄ ነገር እናንተ ስለጋዜጠኞቹ ከምትነግሩን ነገር ጋር አይጋጭም ወይ?” ሲል ይህንኑ ጥያቄ አነሳላቸው፡፡ እሳቸውም ሲጀመር ተልዕኮውን የሚሰጧቸው እነዚሁ ድርጅቶች መሆናቸውን ተናገሩ “መጀመሪያ ተልዕኮ ሰጥተው ያሰማሯቸዋል ሲነቃባቸውና ሲታሰሩ ደግሞ ይሸልሟቸዋል” ሲሉ አለም በሚያከብራቸው በእነዚ ድርጅቶችና በኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች መሀከል ያለውን የሽብር መረብ በልበሙሉነት አስረዱ፡፡ መቼም ይሄ እንደ ኢቲቪ ዶኪመንተሪ አይን ያወጣና ከእውነት በተቃራኒ የቆመ ወለፈንዳዊ ታሪክ ቢሆንም ቢያንስ አንዳዳንድ ታማኝ መሀይሞችን የማሳመን ብቃት የለውም አይባልም፡፡

ሂውማን ራይትስ ዎች የሚያስተዳድረውን የሄልማን ሀሜት የፕሬስ ነጻነት ሽልማትን ከእስክንድር ነጋ፣ ከውብሸት ታዬና ከመስፍን ነጋሽ ጋር በጋራ አሸናፊ በሆነችበት ጊዜም ከውግዘት አልዳነችም፡፡ የባለ ብዕር ስሞቹ ተናዳፊዎች ባዶ ቃለት እንደ ጉድ ተመረቱ፡፡ በፊቱንም በኢትዮጵያ መንግስት ክፉኛ የሚጠላው ሂዩማን ራይትስ ዎችም በአለም ላይ ያሉ ተናካሽ ቃሎች እየተለቀሙ ተወረወሩበት፡፡ ደግነቱ ቃል ጦር ሆኖ የሚገለው እውነትን ሲይዝ መሆኑ እንጂ እነዚህ ቃላት ኢህአዴግ በጥይት ከገደላቸው በብዙ እጥፍ የሚልቁ ሰዎችን ይረፈርፉለት ነበር፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በርዕዮት ጉዳይ ባሳለፈው የመጨረሻ ውሳኔ አቃቤ ህግ  የደረደራቸው መሰረተ ልማት ስለማውደም፣ ሰዎችን ለአሸባሪነት ስለመመልመል፣ በአሸባሪነት የተገኘ ገንዘብ ስለመጠቀምና ስለማዘዋወር የሚያትቱ ክሶችን አለአንዳች ማስረጃ የቀረቡ ናቸው ብሎ ውድቅ ማድረጉ አቶ ሽመልስ ከማልን ከውሳኔውም በኋላ “ርዕዮት የታሰረችው መሰረተ ልማት ልታወድም ስላሴረች ነው” ከማለት አላገዳቸውም፡፡ በዚህ አልረካ ያሉት እኚህ ሰው “ርዕዮት አምደኛ እንጂ ጋዜጠኛ አይደለችም” ሲሉ  የመጨረሻውን የክህደት ቃል ለኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ሰጡ፡፡ ይህን ሳይ “አቶ ሽመልስ ዳኛ ነበሩ እንጂ የህግ ባለሙያ አይደሉም” ብላቸው ከት ብለው እንደሚስቁ በመገመት እኔም በእሳቸው አስተያየት ፍርፍር ብዬ ከመሳቅ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ የሳቸውን አስተያየት ያነበበ አንድ ወዳጄ ንድድ ብሎ “መለስ ጋዜጠኞቹ እያለ አይደለም እንዴ የሚያወራው ይሄኛው ምን ቤት ነው ለነገሩ አሁን ያስቸገሩት ታግለው የመጡት አይደሉም፤ ኢህአዴግ ሲገባ የአበባ ጉንጉን ይዘው የተቀበሉትም አይደሉም፤ አሁን ያስቸገሩት ኢህአዴግ ስልጣኑ ላይ ተደላድሎ መቀመጡን ካረጋገጡ በኋላ እንደግፍሀለን ብለው የተደገፉት ናቸው፡፡” ብሎ አስፈግጎኛል፡፡

እስካሁን የተባለው ሁሉ ሀሰት ስለሆነ ብቻ የስም ማጥፋት ዘመቻው ያለምንም ውጤት ቀርቷል ማለት አይቻልም፡፡ የእስራኤልን የነጻነት በዓል አስመልክቶ ቢኢትዮጵያ ያለው ኢምባሲ ባዘጋጀው እራት ግብዣ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሽብር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብሎ የተካሄደባቸው ልዩ ፍተሻና ክትትል የዘመቻው ውጤት አካል ነው፡፡

አሁን የመንግስታቱ ድርጅት አካል የሆነው ዩኔስኮ ለርዕዮት የሰጠው ሽልማት ግን በብዙ መልኮች ከበፊቶቹ ይለያል፡፡ ይህ ሽልማት ኢትዮጵያ አባል በሆነችበት የመንግስታቱ ድርጅት የሚሰጥ በመሆኑ ኢትዮጵያም በተዘዋዋሪ መልኩ የሸላሚዎቹ አካል ከሆን አታመልጥም፡፡

ከሁሉ በላይ ኒዮሊበራል ምንትስ ለሚባል የተለመደ ፍረጃና ማጣጣል የማይመችና በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ግንባር ላይ የታተመውን የአሸባሪነት ማህተም የሚደመስስ  በመሆኑ ለርዕዮት ብቻ ሳይሆን ለነጻ ጋዜጠኞች ሁሉ የተለየ ትርጉምና ጥቅም ያለው ሽልማት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህን የሚያገናዝብ ጭንቅላት ያልታደሉት ባለ ብዕር ስሞቹ ተሳዳቢዎች የአልሞት ባይ ተጋዳይ ብዕራቸው የሚያመርታቸውን ባዶ ቃላት በአዲስ ዘመን ገጽ 3 ላይ ለመመልከት መጓጓቴን አልደ ብቃችሁም፡፡

ቺርስ!!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s