የማይገድል በሽታ የተጣባዉ የተቃዉሞ ፖለቲካችን (መስከረም አበራ)

ሃገራችን ኢትዮጵያ ረዥም የመንግስትነት ታሪክ ቢኖራትም የታሪኳን ብዙ ክፍል የሚይዘዉ በፊዉዳላዊ የአስተዳደር ዘይቤ ያሳለፈችዉ ዘመን ነዉ፡፡ የፊዉዳሊዝም ረዥም እድሜ ማስቆጠር ደግሞ ሃገሪቱን ወደ ፓርቲ ፖለቲካ እንዳትገባ፣ የሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዳትገነባ እንቅፋት ሆኖ ፍዳዋን አርዝሞታል ፡፡ የፊዉዳላዊዉ ስርአት ማገር የነበረዉ የነገስታትን ”ስዩመ እግዚብሄርነት” ይሰብክ የነበረዉ ማደንዘዣም ህዝቡን ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ እንዳያማትር ሸብቦ ለረዥም ዘመናት እሽ ባይ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ይህ ባለ ረዥም እድሜ የእሽባይነት ፖለቲካዊ ባህል አሁንም አሻራዉ አለ፡፡ ዛሬ ድረስ መንግስት ሁሉን ማድረግ የሚችል ጉልበተኛ፣ ህዝብ ደግሞ መንግስት የሚያደርገዉን ሁሉ አጎንብሶ አሜን ማለት ያለበት አድርጎ የሚያስበዉ የህዝባችን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ይህ የመታዘዝ ፖለቲካዊ ባህላችን ዘግይቶም ቢሆን የተጀመረዉን ፖለቲካን የማዘመን፣ ከሁሉም በላይ ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ የሚደረገዉን እንቅስቃሴ በተፈለገዉ ፍጥነት እንዳይሄድ አድርጎታል፡፡
የፓርቲ ፖለቲካ ጅማሮ
የፊዉዳሉን ስርአት ለመጣልእና በእግሩ የሰለጠ ፖለቲካዊ ስርዓት ለማምጣት ይደረግ ከነበረዉ ትግል ብቅ ያለዉ መኢሶን ለመጀመሪያጊዜ የፓርቲ ፖለቲካን ለሃገራችን አስተዋወቀ፡፡ በመቀጠልም በሃገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ትልቅ አሻራ ማስቀመጥ የቻለዉ ኢህአፓ ተከተለ፡፡ ይህን የቀዳሚነት ነገር በተመለከተ የሁለቱም ፓርቲ አባላት(insiders) በሚፅፏቸዉ መዛግብት እናት ፓርቲያቸዉን ቀዳሚ ደርጋሉ፡፡ የሆነ ሆኖ የጅማሬያቸዉን ጊዜ ያጠኑ ገለልተኞች መኢሶንን ቀዳሚ ያደርጋሉ፡፡ በህዝብ ልቦና ዉስጥ በመግባት እና ተከታይ በማብዛቱ በኩል የታየ እንደሆነ የኢህአፓ ተፅኖ ፈጣሪነት ጎላ ይላል፡፡
ከሁለቱ ፓርቲዎች መፈጠር ጀምሮ የሚቆጠር እድሜ ያለዉ የሃገራችን የፓርቲ ፖለቲካ በአጭር እድሜዉ ብዙ ህማማትን አስተናግዷል፡፡የፖለቲካ ትግል ማለት መጋደል እሰኪመስል ድረስ በዉሃ ቀጠነ የብዙዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ እስከዛሬ ያልለቀቀን ፖለቲካን እንደ ተከሰተ ሰይጣን የመፍራት አባዜያችን መነሻ ምክንያትም ይሄዉ መተላለቅ ነዉ፡፡ የፓርቲ ፖለቲካችን ጅማሮ ሳንካዉ የበዛ፣ መዘዙም እስካሁን የሚመዘዝ ስለሆነ ስንት አመት ተሻግሮም የዛሬዉን ፖለቲካችንንም ታሞ አይድን ድርጎታል፡፡
የጥግ ፖለቲከኝነት ልክፍት
የሰዉ ልጅ አንድን ሁኔታ በተለያየ መንገድ የመረዳት ዝንባሌ ያለዉ ፍጡር ነዉ፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ፓርቲዎች ጥላ ስር ያሉ ግለሰቦች ምንም ሃገርን ፈቀቅ የማድረግ ተመሳሳይ መዳረሻ ቢኖራቸዉ ወደዛ ግብ ለመድረስ የሚመርጡት መንገድ ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህን የአስተሳሰብ መለያየት ጠላትነት አድርጎ መረዳት፣የተለየ ሃሳብያለዉን ሰዉ የሃገር ልጅ ወገንነቱን እንኳን ዘንግቶ እርጉም ፍጡር ማድረግ የጥግ ፖለቲከኝነት መለያዉ ነዉ፡፡ከራስ እምነት እና ሃሳብ ዉጭ ያለን ሀሳብ በሙሉ ዉጉዝ አድርጎ ማየት ፣ የከእኛጋር ያልሆነ ሁሉ ከጠላታችን ጋር ነዉ ፈሊጥም መሃለኛ ሃሳብ እንዳይደመጥ ይከለክላል፡፡ “መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል” እያስባለ ሁሉንም ወደ ጥግ ይገፋል፡፡
የጥግ ፖለቲከኝነት ልማድ በቀደምቶቹ መኢሶንና ኢህአፓ ዘንድ እንደ ፖለቲካዊ ፅናት መገለጫም ይታይ ነበር፡፡ የአንድ ፖለቲከኛ የአላማ ፅናት የሚለካዉ ለተቀናቃኝ ፓርቲ አባል ባለዉ እስከማጥፋት የደረሰ ፅንፈኝነት ጭምር ነበር፡፡ይህ የእርስ በርስ መባላት በጋራ እንቃወመዋለን ለሚሉት ንጉሳዊም ሆነ ወታደራዊ አገዛዝ ጉልበት እንደሚሆነዉ ብዙ ላነበቡት የወቅቱ ታጋዮች እንዴት እንደተሰወረ የሚያዉቅ የለም፡፡ ይህ የበጀዉ ደርግ ኢህአፓን እሰኪያጠፋ መኢሶንን ወዳጅ እያደረገ በመጨረሻ ሁለቱንም አጥፍቶ ሃገሪቱን በአንድ አስተሳሰብ ለአስራ ሰባት አመት ነዳት፡፡ ራሱም በቅጡ የማያዉቀዉን የሶሻሊዝም ርዕዮተ-አለም እየተንተባተበ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲግት፣ሃገሪቱንም ወደ ማትወጣበት ማጥ እንድትገባ እና ዛሬ የሆነዉ ሁሉ እንዲሆንባት በዋናነት የመኢሶን እና ኢህአፓ ፅነፈኝነት ዋነኛዉ ምክንያት ነዉ፡፡ የሆነዉ ሆኖ የእነዚህ ፓርቲወች አባላት ለሃገራቸዉ ሲሉ ደርግን ከመሰለ እግሩ ደም ለማፍሰስ ከፈጠነ አካል ጋር እንኳን ለመተናነቅ ወደኋላ የማይሉ፣ በሃገራቸዉ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የማይደራደሩ፣ ሃገር ወዳዶች እንደነበሩም መረሳት የለበትም፡፡
“ታጋይ የህዝብ ልጅ” እያለ ለራሱ እያዜመ ወደ መሃል ሃገር የገሰገሰዉ ኢህአዴግ ዘረጋሁ ያለዉ የመድበለፓቲ ፖለቲካ ሃራችንን ከብዙ አመት የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ወደ የፓርቲዎች ጋጋታ ዘመን አድርሷታል፡፡ አረረም መረረም ፓረቲዎች መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ የሃገር እጣፋንታ ያሳሰባቸዉ ዜጎችም ይሆናል ያሉትን የፓርቲ ፕሮግራም ነድፈዉ ፓርቲ በመመስረት ለኢህአዲግ የሰላማዊ ትግል ጥሪ መልስ ሰጡ፡፡ ለትግሉ ሲሉም እድሜያቸዉ ገፋ ያሉት ከነሽበት ሽምግልናቸዉ ከመታሰር እስከ መደብደብ የደረሰ ዋጋ ከፍዋል፡፡ ወጣቶቹም መልሰዉ የማያገኙትን የወጣትነት ጊዜያቸዉን በእስር እንዲያሳልፉ ወደዉ ፈቅደዋል፡፡ ከእስር እንግልቱ ባለፈ እነሱ የሚያዉቁት ብዙ ፈተና እንደሚገጥማቸዉ መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ ሁሉ ልዕልናቸዉ ባለዉለታችን ናቸዉና ለልፋት ድካማቸዉ እዉቅና፣ ክብር መስጠት ተገቢ ነዉ፡፡
ከምስጋና መወድሱ ስንመለስ ግን የዘመኑ ተቃዉሞ ፓርቲ ታጋዮች የሚመሩት ትግል ህማማቱ ብዙ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ከጠዋቱ ዋኖቻቸዉን ተጣቁሮ የነበረዉን የጥግ ፖለቲከኝነት ልክፍት እነሱም ይጋሩታል፡፡ የዘመንኞቹ ጥግ መያዝ ደግሞ ግላዊ አስተሳሰብን ብቻ ትክክለኛ አድርጎ እስከማሰብ ይደርሳል፡፡ እነሱ በግል ጥሩ ነዉ ብለዉ ካሰቡት ዉጭ የሚያስብ የራሳቸዉ ፓርቲ አባልም ሆነ አመራር አይመቻቸዉም፡፡የሃሳብ ልዩነታቸዉ መዳረሻም መሃከለኛ ሃሳብ ሳይሆን እግድ፣መወነጃጀል እና ወደ ብዙ ትንንሽ ፓርቲዎች መቀየር ነዉ፡፡
ከግላዊ አስተሳሰባቸዉ የሚቃረን ከሆነ የህዝብ ፍላጎትም ለአንዳንዶቹ ምንም ነዉ፡፡ የቅንጅትን ዉህደት ባለቀ ሰአት ያሰናከለዉ የአንድሰዉ ዉህደቱን አለመቀበልነበር፡፡ የቅንጅት ዉህደት ደግሞ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ማለት እንደነበረ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ግና ማህትም በእጁ የነበረዉ ግለሰብ ነገሩን አልወደደዉምና የህዝብ ፍትላጎት ምንም ይሁን ምን ግለሰቡ ከፅንፈኛ አቋሙ ፍንክች አላላም፡፡ የነቶሎቶሎ ህብረት
እንደ ኢህአዴግ ራሱን በብዙ መንገድ ያበረታን ገዥፓርቲ ለመገዳደር መተባበር ግድ ይላል፡፡ ትብብሩ ግን በደንብ የታሰበበት፣ ካለመተባበሩ የተሻለ መሆን አለበት፡፡ ሊተባበሩ ጉዞ የጀመሩ አካላት ቢያንስ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መስማማት አለባቸዉ፡፡ ይህ ወሳኝ ቅድመሁኔታ ካልተሟላ ህብረት ሳይፈጥሩ ሁሉም በመሰላቸዉ መንገድ ሄደዉ ቢሞክሩት ሳይሻል አይቀርም፡፡ በዚህ ግንዛቤ የሃገራችንን ተቃዉሞ ፖለቲከኞች ትብብር ስናይ ትብብራቸዉ የነቶሎቶሎ ሲሆን ባረም ተመልሶ ማስተካከሉም ብዙ ሲሰምርላቸዉ አይታይም፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ የቸኮለ ትብብራቸዉን በፈጠነ መሰነጣጠቅ ይደመድማሉ፡፡
የሚገርመዉ ደግሞ ለመሰነጣጠቃቸዉ ጠብ የሚል ቁምነገር ያለዉ ምክንያት ማቅረብ አለመቻላቸዉ ነዉ፡፡ በርግጥ ለመተባበር ጥሩ ምክንያት የሌለዉ ለመበታተኑም አጥጋቢ ምክንያት ባይኖረዉ የሚጠበቅ ነዉ፡፡ ምናልባት ሊወራ የሚችል አንድ የተሻለ ምክያት ሊሆን ይችላል ብየ በግሌ የማስበዉ በ1998 ዓም ፓርላማ በመግባት ና ባለመግባት ተለያን ያሉት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡በተረፈ ለአብዛኛዉ ጠብና ክርክራቸዉ ሰራተኛ መቀጠር ወይ መባረር፣የገቢ ማሰባሰቢያ የዉጭሃገር ጉዞ መፍጠንና መዘግየት፣የፓርቲ ባጀት ማወራረጃ ደረሰኝ ማቅርብ አለማቅረብ፣የቢሮ ኪራይ ዋጋ ማነስ መብዛት ለመሰነጣጠቃቸዉ በቂ ምክንት ሆነዉ ሰምተናል፡፡ አራት ፓርቲዎችን ስምንት ወር ባልሞላ ጊዜ አቀናጅቶ ብዙ ተስፋን ያሰነቀን ቅንጅት አሳዛኝ ፍፃሜ፣ አዕላፍ የሃገር ዉስጥ እና በባህር ማዶ የከተሙ ፓቲዎችን አሰባስቦ የነበረዉ ህብረት የተባለዉ ፓርቲ “ተዉት ተዉት” ተባብሎ መፈራረስ ከላይ ለተባለዉ ነገር ጥሩ ማስረጃዎች ናቸዉ፡፡
የባለፈዉ ሰሞን የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ በአማራ እና በአዲስ አበባ ልሂቃን ተወረርን እሪታ በመድረክ ስም ግንባር ፈጠርን ያሉ ፓርቲዎችን ከሃረግ መዝዛ ያልተዋጀ አብሮነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ የአዲስ አበባ ልሂቃን የሚለዉ ደግሞ አዲስ የመከፋፈያ መንገድ መሆኑ ነዉ፡፡ አቶ ቡልቻ ይህንን አስመልክቶ ለተለያዩ ሚዲያዎች ይሰጡት የነበረዉ ቃለ ምልልስ እና ይፅፉት የነበረዉ ፅሁፍ መድረክ የተባለዉ ግንባር ምን ያህል ማጣራት ያለበትን ነገር ሳያጠራ በጥድፊያ በተዉሸለሸለ ህብረት እንደቆመ አንድ ማስረጃ ነዉ፡፡ ከተቃዉሞዉ ጎራ የተሻለ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንዳላቸዉ የሚናገሩት መድረክን የፈጠሩት ፓርቲዎች ያሉበትን መጠባበቅ እና አለመተማመንም ያሳብቃል፡፡ ከወንዘኝነት ባለፈ አንድ ሊያሳኩት የሚፈለጉት ትልቅ አገራዊ አጅንዳ መኖሩንም እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡ “የኛ ሰፈር ሰዎች ወደስልጣኑ ሰገነት አልቀረቡም” እያሉ ከሚብሰለሰሉ፣ ይሄንንም ትልቅ ጉዳይ አድርገዉ ጮክ ብለዉ ከሚናገሩ አመራሮች ምን ሃገራዊ አጅንዳ ይጠበቃል? እንዲህ አይነቱ ህብረት የት ሊያደርሳቸዉ ጉዞ እንደጀመሩ የሚያዉቁት እነሱ ብቻ ናቸዉ፡፡
ስብርባሪ ፓርቲዎች
መጥራት ያለበትን ሳያጠሩ ህብረት፣ግንባር፣ጥምረት እያሉ ስሙን ወደሚያበዙት አብሮነት የሚያዘግሙት ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎቹ የአብሮነታቸዉ መጨረሻ ወደ ስብርባሪ ፓርቲነት መቀየር እንጂ ገዥዉን ፓርቲ በአጥጋቢ ሁኔታ መገዳደር አልሆነም፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ፓርቲ አመራርነት እየሰሩ ያሉ ሰዎች በአንድ ወቅት በሌላ ፓርቲ ጥላ ስር አብረዉ ሰርተዋል፡፡ ነገርግን አብሮ የማያሰነብት አይነጥላ ተጠናዉቷቸዋልና በየፊናቸዉ የየራሳቸዉን ፓርቲ መስርተዉ ብዙ ድካማ ፓርቲወችን ይመራሉ፡፡ ሃገራችንም ወደ ሶስት ዲጂት እገሰገሰ ያለ ቁጥር ያላቸዉ እንደስለት ልጅ ህመም የማያጣቸዉ ፓርቲዎች ባለቤት ሆናለች፡፡ ይህም ለኢህአዴግ “ተቃዋሚዎች ሃገር ለመምራት አይችሉም” ዜማ አስረጂ ሲሆን ቁጥሩ ቀላል የማይባልን ህዝብ ደግሞ “ኢህአዴግ ይግደለኝ” አስብሎታል፡፡
በድካም ላይ ንትርክ!
የፓርቲ ዲሞክራሲን ከእርስበርስ መቆራቆስ ያልለየዉ ንትርካቸዉ የተቃዉሞ ፖለቲከኞቻችንን ለደጋፊዎቻቸዉ ተስፋ የማይሰጡ፣ለገዥዉ ፓርቲም የማያሳስቡ ባላጋራዎች አድርጓቸዋል፡፡ ንትርኩ እስከ ድንጋይ መወራወር የሚደርስ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ እዚህ ግባ የማይባል ተራ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ በቢሮዋቸዉ ያልተግባቡበትን ነገር አደባባይ አዉጥተዉ ሲዘላለፉ የነሱን ትግል ተስፋ ለሚያደርገዉ ህዝብ ስሜት ለአፍታ የሚጨነቁ አይመስሉም፡፡ አለመግባባታቸዉን በመወራረፍ ካልገለፁት የታገሉ አይመስላቸዉም፡፡
በ2002 ሃገራዊ ምርጫ የስነምግባር ደምቡን በፈረሙት እና ባልፈረሙት መሃከል የነበረዉ ንትርክ ኢህአዴግን ያሳረፈ ነበር፡፡ስነምግባር ደንቡን ፈረምን ያሉት ያልፈረሙትን ወገኖች ትግል “አይረቤነት” የገለጹት “ያለፈበት የኡኡታ ፖለቲካ አራማጆች” በማለት ነበር፡፡ ከ1997 ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ በድርድር ስም ያደረገዉን የሚያዉቀዉ መኢአድ ተመልሶ ከኢህአዴግ ጋር መፈራረሙ መብቱ ቢሆንም በሱ መንገድ አንሄድም ያሉትን እንደዛ ማዉገዙ ግራ አጋቢ ነበር፡፡ “የተፈራረምኩት እስረኞቸን ላስፈታ ነበር ብዙዎቹን አስፈትቻለሁ” ያለዉ መኢአድ ሌሎቹ ሚያስፈቱት እስረኛ ባይኖራቸዉስ? እስረኛ ቢኖራቸዉም የሚያስፈቱበት ሌላ መንገድ አስበዉ ቢሆንስ ?ወይም እስረኛ ከማስፈታት ያለፈ አጅንዳ ቢኖራቸዉስ? ይህን ሁሉ ግምት ዉስጥ ሳያስገባ እኔን ያልተከተለ የተረገመ ይሁን ማለትን ምን አመጣዉ? ሳይዉል ሳያድር ግን በኢህአዴግ ተታለልን ኡኡታዉን የጀመሩት እነዚሁ ፈረምን ባዮቹ ነበሩ፡፡ የልቡን የሰራዉ ኢህአዴግም “ማን ፈርሚ አለሽ”ን ሳይዘፍን አልቀረም፡፡ የራስን የትግል መስመር ማስኬድ የሚቻል ሆኖ ሳለ የሌላዉን ሃሳብ ማክበር ደግሞ ታላቅነት ነዉ፡፡ በተለያየ መስመር ተጉዞ ተመሳሳይ ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻል ማወቅም ከጥግ ፖለቲከኛነት ፈቀቅ ማለትን ይጠይቃል፡፡
በቅንጅት አመራሮች አቶ ሳሳሁልህ ከበደ እና በባልደረባቸዉ አቶ አየለ ጫሚሶ መካከል በተከሰዉ አለመግባባት ሁለቱ አመራሮች በየሳምንቱ በፍትህ ጋዜጣ ላይ እየፃፉ ሲባባሉ የነበረዉ ነገር ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ንትርኩን ያመጣዉ ምክንያት አይረቤነት የምናዉቀዉ ባሁኑ ሰአት ሁለቱ ሰዎች በምን መርህ ተስማምተዉ አብረዉ መስራት እንደጀመሩ ለህዝብ ግልፅ ሳያደርጉ አብረዉ መስራተቸዉን ቀጥለዋል፡፡ መቸም እንደዛ መነታረክ የቻለ ሰዉ ለምን ሰላም እንዳወረደ መናገር አይቸግረዉም፡፡ ንትርካቸዉን ያነበበ ህዝብ ደግሞ መጨረሻቸዉ ምን እንደሆነ ቢያዉቅ አይከፋም፡፡
የፕ/ሮ በየነ በደረሱበት ሁሉ የአጋራቸዉን አቶ የግርማ ሰይፉን ፓርላማ መግባት የሚያወግዙበት ሁኔታም ሌላዉ የንትርኩ ማሳያ ነዉ፡፡የሚገርመዉ ወቃሹ አመራር በ 1998 ዓ.ም ለምን ፓርላማ አትግባ እባላለሁ ብለዉ ፓርላማ መግባት ከሚቀር ህብረትን የሚያክል ግዙፍ ፓርቲ ቢሰነጠቅ ይቀላል ብለዉ ባህር ማዶ ካሉ አጋሮቻቸዉ የተቆራረጡ ሰዉ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ ሰሞኑን እየተጧጧፈ ያለዉ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና በኢ/ር ዘለቀ ረዲ መሃከል የተነሳዉ እንካሰላንቲያም እዚህ የሚያደርስ፣ ተነጋግሮ ለመፍታት የማይቻል ምክንያት ያለዉ ሆኖ አይደለም፡፡ እንደዉ ግዙፍ ነገር ቢኖር እንኳን ምክንያታቸዉን አጠር አድርገዉ ለህዝብ አሳዉቀዉ ዝርዝሩን እዛዉ ተነጋግረዉ መፍትሄ የሚሉትን ቢያደርጉ በተሻለ፡፡ አሁን የተያዘዉ ሆድ ባዶ እስኪቀር መነጋገር ያስገምታል፡፡ የመኢአድ ደግሞ ይብሳል፡፡ ከመለመዱ የተነሳ የነሱን ንትርክ ነገሬ ብሎ የሚከታተል ሚዲያም እየጠፋ ነዉ፡፡
ስራ በሚሰራ ሰዉመሃል አለመግባባት ቢኖር የሚጠበቅ ነዉ፡፡ በሃገራችን ተቃዋሚዎች ሁኔታ ግን የሚሰራዉ ጉልህ ነገር ሳይታይ የንትርኩ ዜና ግን ከእግድ ተረፉትን ትቂት ጋዜጦች ገፆች ያጣበበ መሆኑ ነዉ መጥኔ የሚያሰኘዉ፣ ግራአጋብቶ ተስፋ የሚያስቆርጠዉ፡፡
ገራገር ትግል
የሃገራችን ተቃዋሚዎች ከእርስ በርስ ንትርክ በተረፈዉ ጉልበታቸዉ ፈርጣማዉን ኢህአዴግ ለመታገል መሞከራቸዉም አልቀረም፡፡ እነሱ በዛለ ጉልበታቸዉ ሲዉተረተሩ መበለጥን የማይወደዉ ኢህአዴግ ደግሞ ብዙ እርቀት እንዳሄዱ እገራቸዉ ላይ ድንጋይ ማሰሩን ተያይዞታል፡፡ ይህ ደግሞ ትግላቸዉን እያደር ገራገር አድርጎታል፡፡ ይህንኑ ለክፉ የማይሰጥ ህልዉናቸዉን እንኳን ሃገሬዉ የዉጭሃገር ፖለቲከኞችም ያዉቁታል፤ እራሳቸዉ ፓርቲወቹም ምርጫ ላይ የምንሳተፈዉ እናሸንፋለን ብለን አይደለም ሲሉ “በደንብ” ይገልፁታል፡፡ ምን አይነት መራጭ ይሆን ይህን ተሸናፊነታቸዉን ከምርጫ በፊት በራሳቸዉ አፍ ላወጁ ፓርቲዎች ድምፁን የሚሰጠዉ?እንደማያሸንፉ ቀድመዉ እያወቁ እሱንም እየተናገሩ መወዳደርን ምን ይሉታል? ወይ ስፖርታዊ ዉድድር ቢሆን እንኳን የራስን ሰአት ለማሻሻል፣ ወቅታዊ አቋሙን ለመፈተሸ ሊባል ይችላል፡፡
“ያሳስበናል” ፣ “እናወግዛለን” የሚሉ አይነት ቃላት የበዙበት የአቋም መግለጫ በማዉጣት የቆረበ መሰለዉ የትግል ስልታቸዉም ሌላዉ የገራገር ትግላቸዉ ምስክር ነዉ፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ደግሞ ለዚህ ለተለመደዉ የአቋም መግለጫቸዉ ጆሮ ጠገብ ሆኗልና ነገሬ ሲለዉም አይተን አናወቅም፡፡ ግንቦት 7 1997 ዓም የተከለከለዉ ሰላማዊ ሰልፍ የማደረግ መብት ድፍን ስምንት አመት ሙሉ ሳይነሳ የቆየዉ በከልካዩ ኢህአዴግ “ጉብዝና” ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዎቹ ገራገር ተገዳዳሪነትም ጭምር ነዉ፡፡
የተቃዉሞ ፖለቲከኞቻችን የህዝብን ቀልብ የሳቡና ለነሱ ደግሞ ፖለቲካዊ ትርፍ ሊያስገኙላቸዉ የሚችሉ ወቅታዊ አጀንዳዎችን ነቅሶ አዉጥቶ እና አማራጭ መንገድ አሳይቶ ደጋፊ የማብዛት ችግራቸዉም የሚታይነዉ፤ ለምሳሌ እንደ ኑሮዉድነት፣ ስደት፣መፈናቀል፣መጠነ ሰፊ እስር፣ በአረቡ አለም በስደት የሚገኙ ዜጎችን መብት ያለማስከበር፣ የፍትህ አካላት ነፃነት ጉዳይ፣ የህዝብን ሚዛናዊ መረጃ የማግኘት መብት ማጣት፣የምሁራን ፍልሰት ያሉ የገዥዉን ፓርቲ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ የመከወን ሳንካዎ ወደ ጠረጲዛ በማምጣት ህዝቡን የማታገል ክፍተት አለባቸዉ፡፡ እንደዉም በዚህ ረገድ ኢህአዴግ የእነሱን ትልቅም ሆነ ትንሽ ስህተቶች በማጉላት ሃገር የመምራት ብቃት እና ጥንካሬ የሌላቸዉ ሲል ያጠለሻቸዋል፡፡ ድክመታቸዉን ጠንካሬዉን ለማሳየት ተጠቅሞበት የማይናቅ ፖለቲካዊ ትርፍ አግኝቶበታል፡፡
አንድ ሃገራዊ ምርጫ ካለፈ በኋላ ሌላ ምረጫ ሊመጣ ትቂት ወራት እስኪቀሩት ድረስ የሚወርሳቸዉ ከሞት የበረታ ዝምታ የኢትዮጵያ ህዝብ ከነመኖራቸዉ እስኪረሳ ያደርሰዋል፡፡ ምርጫ ደርሶ ብቅ ሲሉ ደግሞ “የምንዎዳደረዉ ልናሸንፍ አይደለም” ብለዉ ቁጭ ይላሉ፡፡ ሌላዉ አስገራሚ ነገር ደግሞ ኢህአዴግ በድርድር ስም የሚዘረጋባቸዉ ወጥመድ ዉስጥ እንደ የዋህ እርግብ ሰተት ብለዉ የሚገቡት ነገር ነዉ፡፡አንድጊዜ መበለጥ መችም ያለ ነዉ፤ ሁልጊዜ ኢህአዴግ ድርድርን የሚረዳበትን ስነልቦና መረዳት አለመቻል ግን ግር ያሰኛል፡፡ በ2002 ዓም መዳረሻ በመኢአድ እና በኢህአዴግ መሃከል የተደረገዉን ድርደር እና ከምርጫዉ በኋላ ሲሰማ የነበረዉን የመኢአድ የተታለልኩ እንጉርጉሮ ማስታወስ ይቻላል፡፡
ተቃዋሚዎች የአባላት እና ደጋፊዎቻቸዉን ፖለቲካዊ ንቃት ከማሳደግ አንፃር ከታየ ደግሞ ምንም ስራ አልሰሩም ለማለት ያስደፍራል፡፡ በእዉቀት ላይ ያልተመሰረተ ትግል ዘላቂነቱ አስተማማኝ አይደለምና ፓርቲያቸዉ የቆመበትን ርዕዮተ-አለም አባላቶቻቸዉም ሆኑ ሰፊዉ ህዝብ እንዲያዉቅላቸዉ አዉቆም እንዲከተላቸዉ ሰፊ ስራ መስራቱን ችል ባይሉ መልካም ነበር ግን ይህ ሲሆን አይታይም፡፡

ከአያያዝ ይቀደዳል
በ1997 ምርጫ ኢህአዴግን እንደዛ ሁለት ነብር እንዳየ ሰዉ ያስደነገጠዉ ተቃዋሚዎቹ በአጭር ጊዜ ማስከተል የቻሉት የደጋፊ ብዛት እንጂ የታጠቁት መሳሪ አልነበረም፡፡ህዝቡ እዉነትም ተከትሏቸዉ ነበር፡፡ነገር ግን የፓርቲዎቹ በየቀኑ ለብዙ መሰነጣጠቅ በህዝቡ የሞቀ የለዉጥ ፍላጎት ላይ ቀዝቃዛ ዉሃ ቸለሰበት፡፡ በትቂት ጊዜ ያገኙትን የህዝብ ወገንተኝነት ከዉሃ ቀጠነ ንትርካቸዉ ሲመለሱም፣ ተሰነጣጥቀዉ ሲጨርሱም በነበረበት የሚያገኙት ስለመሰላዉ ይሆናል ከወርቅ የከበረዉን የህዝብ ድጋፍ ጠብቀዉ ማቆየት ያልቻሉት፡፡ ከአያያዝ ተቀዶባቸዋልና ከክፍፍላቸዉ እና ንትርካቸዉ መለስ ሲሉ ማስፈራት ሆኖላቸዉ የነበረዉን የህዝብ ድጋፍ መልሰዉ ማግኘት አልቻሉም፡፡
ፍቅር እንደገና አይገኝምና
በተቃዋሚ ፓርቲዎች መንደር የሚስተዋለዉን የማያስደስት የፖለቲካ ዘይቤ ያጤነዉ ህዝብ በ ሶስተኛዉ ሃገራዊ ምርጫ ተቃርበዉበት ወደ ነበረዉ ስልጣን አለመምጣታቸዉን እንደወደደዉ በህዝብ መሃል ሚኖር ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ለተቃዉሞዉ ጎራ መዳከም እና አሁን ያለበት ዝቅታ ላይ መድረስ የኢህአዴግን ብርቱ እና ረጂም እጅ ሚና የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ገዥዉ ፓርቲ በተቃዋሚወች ላይ ለተቀዳጀዉ “አብረቅራቂ” ድል የራሳቸዉ የተቃዋሚወች አስተዋፅኦ ቢበዛ እንጂ አያንስም፡፡ አሁን በሚታየዉ መልኩ የህዝብ ልብም ጆሮም ከተቃዋሚዎች መንደር እያደር ርቋል፤ እንደ አሜባ መቆራረጣቸዉም ሆነ ተጣመርን፣ ተዋሃድን ማለታቸቸዉ፣ ማኒፌስቶ መፃፍፋቸዉ፣ ኢህአዴግ በገዛ ገንዘባችን እንኳን ሆቴል እራት እየበላን ገቢ ማሰባሰብ ከለከለን አይነት የስሞታ ጋጋታቸዉ ዛሬ ላይ ህዝቡን ያናድደዉ ይሆናል እንጂ አያሳስበዉም፡፡ የህፃን አዋቂዉ በኳስ ፍቅር መክነፍስ በሃገሩ ፖለቲካዊ ሁለመና ተስፋ መቁረጥ ያመጣዉ ሳይሆን ቀራል?
ታቦቱን ማስመለስ
መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚተርከዉ በኦሪት ዘመን ለእስራኤል ጉልበት የነበረዉ የአምላካቸዉ ቃልኪዳን ታቦት ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ግን በራሳቸዉ ጥፋት የማስፈራታቸዉ ሚስጠር፣ የድልአድራጊነታቸዉ ዋስትና የነበረዉን ታቦት ጠላት ማረከባቸዉ፡፡ ከምርኮዉ በኋላ የእስኤል ማስፈራት ቀርቶ በመንደራቸዉ መፍራት መበረገግ በረታ፡፡ ወደቀድሞዉ ድል አድራጊነታቸዉ ለመመለስ ታቦታቸዉን ማስመለስ ነበረባቸዉ፡፡ አሁን ተቃዋሚዎች ያሉበት እዉነታ ከብዙ ዘመናት በፊት የነበረዉን የእስራኤላዊያንን ታሪክ ይመስላል፡፡ ተቃዋሚዎች የማስፈራታቸዉ ሚስጥር የነበረዉ ህዝባዊ አጋርነት እና ድጋፍ ዛሬ አብሯቸዉ ባለመሆኑ በሚገዳደሩት ኢህአዴግ ፊት ሚዛናቸዉ ቀሏል፣ ጥላቸዉ ተገፏል፣ የማይገድል በሽታ ተጠናዉቷቸዋል፡፡ ታቦታቸዉን ለማስመለስ ተቃዋሚዎች የርስበርስ እሰጣገባቸዉን ትተዉ ትልቁን የሃገር ጉዳይ ማየት የሚችል አይን፣የተገዳዳሪያቸዉን ፈርጣማነት የሚመጥን ታግሎ የማታገያ ስልት፣ የኮበለለዉን የህዝብ ልብ መመለስ የሚችል አጠቃላይ ትቋማዊ ለዉጥ ያስልጋቸዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s