የጸረ ሽብር አዋጁ ይሰረዝ ሲባል…(በስለሺ ሐጎስ)

???????????????????????????????አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ፓርላማ በ2001 ዓ.ም ያጸደቀው የጸረ ሽብር ህግ (አዋጅ 652) እንዲሰረዝ በይፋ የሚጠይቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ማወጁን ተከትሎ የጸረ ሽብር ህጉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ስር አዲስ መነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን ችሏል፡፡ መንግስት የአንድነትን ጥያቄ ሽብርተኝነትን ከመደገፍ ጋር አያይዞ ያቀረበው ሲሆን የሚሚ ስብሀቱን ክብ ጠረጴዛ ጨምሮ አንዳንድ ሚዲያዎችና ግለሰቦች አንድነት ፓርቲንም ሆነ አዋጁ እንዲሰረዝ የሚጠይቁ ዜጎችን በአሸባሪነት ከመፈረጅ አልፈው መንግስት በዝምታ ሊመለከታቸው አይገባም የሚል የይታፈሱልን ጥሪ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡
እነዚህን ኃይሎች ወደ ፍረጃና ወደ አሳፋሽነት የገፋቸው ዋነኛ ምክኒያት አሁን ያለውን የጸረ ሽብር አዋጅ እንዲሰረዝ መጠየቅ ሽብርን እደግፋለሁ ወይም ጨርሶ የጸረ ሽብር ህግ አያስፈልግም የሚል ትርጓሜ ስለሰጣቸው መሆኑን ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም እነዚህ ሁለት ሰሞነኛ ተቃርኖዎች (የአንድነት ፓርቲ የይሰረዝልን ጥያቄ እና የነ ሚሚ ስብሀቱ ይታፈሱልን ጥሪ) ናቸው፡፡
የጸረ ሽብር ህጉ ይሰረዝ ማለት በርግጥ ሽብርተኞች በሀገራችን ላይ እንዳሻቸው ይፈንጩ ማለት ነውን? አሁን ያለው የጸረ ሽብር አዋጅስ መንግስትና ደጋፊዎቹ እንደሚሉት ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ እንከን የለሽ ህግ ነው? ይህ ጽሑፍ በዋናነት በእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ላይ ያተኮሩ አንዳንድ የመወያያ ሀሳቦችን ለመሰንዘር ይሞክራል፡፡
ሽብር ሲባል…
ሽብርተኝነት ረዥም ዕድሜ ያለው አለም አቀፍ የወንጀል ክስተት ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሁሉም ዘንድ ቅቡል የሆነ አንድ ወጥ ትርጓሜ አላገኘም፡፡ ይሁን እንጂ የሽብርተኝነት ድርጊት አጸያፊና ዘግናኝ ወንጀል በመሆኑ የማይስማማ የለም፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች የሚሆኑት በአብዛኛው ንጹኃን ሰዎች መሆናቸው ሲታሰብ ድርጊቱ ከደረቅ ወንጀልነትም ይዘላል፡፡
ለኛለኢትዮጵያውያን ደግሞ ሽብርተኝነት ከምንም በላይ የከፋ ተግባር ነው፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ሽብርተኝነት ማለት የሰው ልጆች የሚያከብሩት ህግ የሚፈሩት አምላክና የሚጸጽታቸው ህሊና ሲያጡ የሚፈጽሙት የመጨረሻው ሀጢያት ነው፤ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
የራስን አላማ ወይም ፍላጎት ለማሳካት ሲባል የንጹኃንን ህይወት የሚቀጥፍና ህዝባዊ ተቋማትን የሚያወድም ተግባር መፈጸም በምንም አይነት መለኪያ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የሽብርተኝነት ድርጊት በምንም ምክኒያት፣ በየትም ቦታ፣ በማንኛውም ሰው ላይ እንዳይፈጸም አለም ሁሉ የዘመተበት ወንጀል የሆነው፡፡
ጸረ ሽብር ሲባል…
ይህ ወቅት ከመቼውም በላይ አለም አቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻው ተፋፍሞ የቀጠለበት ጊዜ ቢሆንም ዘመቻው ሽብርን ሊያጠፋው ቀርቶ ጋብ ሊያደርገው አለመቻሉ አሳዛኝ እውነት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በመከወን እንዲጠመዱ አስገድዷቸዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከሽብር ስነልቦና ጋር የማይተዋወቅና ሽብርተኝነትን የሚጸየፍ ህዝብ የሚኖርባት ሀገር መሆኗ የጸረ ሽብር ዘመቻውን ከመቀላቀል አላገዳትም፡፡ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለሽብርተኞች የተጋለጠ መሆኑና አሜሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ላወጀችው የጸረ ሽብር ዘመቻ የቀጠናው ግምባር ቀደም አጋር በመሆኗ የዘመቻው ንቁ ተሳታፊ ከሆኑ ሀገራት ምድብ ተቀላቅላለች፡፡ ከአራት አመት በፊትም ለብዙ ትችቶች የተጋለጠውን አወዛጋቢ የጸረ ሽብር ህግ (አዋጅ 652) አጽድቃ ተግባር ላይ አውላለች፡፡
ሽብር አጸያፊና ዘግናኝ የወንጀል ድርጊት እንደመሆኑ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማጥፋት የሚደረጉ አለም አቀፍም ይሁን ሀገር አቀፍ ትግሎችን ሽብርን የሚኮንኑ አካላት ሁሉ ሊደግፉና ሊተባበሩ የሚገባ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስከዛሬ ከተደረጉና አሁንም እየተደረጉ ካሉ የጸረ ሽብር ዘመቻዎችም ሆነ በአለምአቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ጸድቀው ተግባር ላይ ከዋሉ ህጎች መሀከል አብዛኞቹ፣ በተለያዩ አካላት የመረረ ተቃውሞና ትችት ተነስቶባቸዋል፡፡ በዘመቻው ግምባር ቀደም የሆኑ ሀገራትን ሳይቀር ለውዝግብ የዳረጉ የጸረ ሽብር ህጎችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡
ምስራቅ አፍሪካን ከሽብርተኞች ለማጽዳት አሜሪካና ኢትዮጵያ በአጋርነት እየሰሩ ያሉ ወዳጅ ሀገራት ሆነው ሳለ የኢትዮጵያን የጸረ ሽብር ህግ በጥብቅ ከሚተቹ ሀገራት መሀከል አንዷ አሜሪካ ናት፡፡ ህጉን ከመተቸትም ባለፈ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ኢትዮጵያ አሸባሪ ብላ ያሰረቻቸውን ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንድትፈታ መጠየቁ በጸረ ሽብር ተግባራት ላይ ያለው ውዝግብ ዛሬም ድረስ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው፡፡
የተቃውሞዎቹና የውዝግቦቹ ዋነኛ መነሻ፣ ሽብር ማለት ምን ማለት ነው? የሽብርተኝነት ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው? አሸባሪስ ማነው? በሚሉ አበይት ጥያቄዎች ላይ የጸረሽብር ዘመቻው ተዋናዮች ስምምነት ላይ ሊደርሱ ያለመቻላቸው ነው፡፡ እነዚህን አበይት ጥያቄዎች በመበየን ሂደት ላይ ሽብርተኝነትን ከሰላማዊ የፖለቲካ ተቃውሞዎች፣ ከጸረ ጭቆና እንቅስቃሴዎችና በህግ ዕውቅና ካገኙ ሰብአዊ መብቶች ጋር የሚያጣርሱ በርካታ መንግስታት በመኖራቸው ውዝግቡ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡
የጸረ ሽብር አዋጁ ይሰረዝ ሲባል…
የኢትዮጵያ ፓርላማ ካጸደቃቸው አዋጆች መሀከል የጸረ ሽብር አዋጅ በመባል የሚጠራው አዋጅ 652 አንዱ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ከረቂቅነቱ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በርካታ ውግዘቶችና ተቃውሞዎችን እያስተናገደ አመታትን ዘልቋል፡፡ የአዋጁ አንቀጾች ቴክኒካዊ የህግ ትርጓሜ ያለቅጥ መለጠጥ ብቻ ሳይሆን አዋጁ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ያለው አተገባበር ለክፉ ተቃውሞ ዳርጎታል፡፡ አዋጁ ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያገኙ መብቶችን ይጋፋል ብቻ ሳይሆን መንግስት ተቃዋሚዎቹንና ተቺዎቹን ለማጥቃት እንደ መሳሪያ እየተጠቀመበት እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
እንዲህ አይነት ተቃውሞዎች ሲነሱ መንግስት በአዋጁ ላይ ተግባራዊ ማሻሻሎችን ለማድረግ በሚያስችል ሆደ ሰፊነት ወደ መግባባት የሚያመጡ ውይይቶችን ማካሄድ፣ ሽብርን የመከላከል አንዱ አካል እንደሆነ ማመን ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ማጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ የጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ተቃውሞ ያስነሱትንና አዋጁ እንዲሰረዝ ለመጠየቅ ህጋዊና ሰላማዊ የህዝብ ንቅናቄ ውስጥ የተሳተፉትን አካላት በአሸባሪነት ለመፈረጅ ሲዳዳው ተመልክተናል፡፡ ይህ አይነቱ የመንግስት አተያይ አዋጁ ያስከትላል ተብሎ ከሚሰጋው የከፋ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ ባህሪ ነው፡፡
በአለም ላይ የተከሰቱ ሁነቶች የሚያሳዩን ሀቅ ጥቂት የማይባሉ አምባገነን መንግስታት በጸረ ሽብር ዘመቻ ስም በሚገዙት ህዝብ ላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ነው፡፡ አንዳንዶቹም በሽብር ጥቃት ሊደርስ ከሚችለው አደጋ የከፉ ወንጀሎች ናቸው፡፡ የሊቢያ መሪ የነበረው ሟቹ መሀመድ ጋዳፊ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበትን የሀገሩ ዜጎች ሲጨፈጭፍ አሸባሪ ናቸው በሚል ሰበብ ነበር፡፡
ተቃውሞ የሚያነሱባቸውን የነጻነት ታጋዮች በአሸባሪነት ፈርጀው የሚያሳድዱ፣ የሚገሉና የሚያስሩ መንግስታት መታየታቸው የጸረ ሽብር ዘመቻ የተባለ ሁሉ የጸረ ሽብር ዘመቻ አለመሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ዛሬ አለም ሁሉ የነጻነትና የሰላም ተምሳሌት አድርጎ የሚያያቸው ማህተመ ጋንዲና ኔልሰን ማንዴላ ያኔ በሚታገሏቸው ገዢዎች በአሸባሪነት መፈረጃቸው ደግሞ አሸባሪ የተባለ ሁሉ አሸባሪ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡
በመሆኑም ማናቸውም የጸረ ሽብር ህጎች ሲጸድቁም ሆነ ተግባር ላይ ሲውሉ ለታሰበላቸው ሽብርን የመከላከል አላማ ብቻ እንዲውሉ መወትወትና ከአላማቸው በተቃራኒ ላለ ተግባር ሲያገለግሉ መቃወም ሽብርን ከመደገፍ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም የጸረ ሽብር ህግ ከጸደቀበት አላማ በተቃራኒ ሲውል ከሽብር ጥቃቶች የማይተናነስ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ተቃውሞው ሽብርን የመከላከል አንዱ አካል ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አንጻር አንድነት ፓርቲ የጸረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ያነሳውን ጥያቄ ለመደገፍም ሆነ ለማውገዝ የጥያቄውን መነሻ ሰበቦች መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ድጋፉና ውግዘቱም መሆን ያለበት በጥያቄው መነሻ ሰበቦች ላይ ብቻ እንጂ አዋጁ ይሰረዝ የሚል ጥያቄ መነሳቱን በራሱ እንደ ስህተት ማየትና አሸባሪነትን ከመደገፍ ጋር ማያያዝ ከምክኒያትም ከዕውቀትም ጋር የተጣላ አካሄድ ይሆናል፡፡
እንከን-የለሽ አዋጅ ሲባል
መንግስት ስለዚህ አወዛጋቢ አዋጅ እንከን የለሽነት ብዙ ጊዜ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ህጉ የዳበረ የዴሞክራሲ ልምድ ካላቸው ሀገራት መቀዳቱን በመግለጽ አዋጁ ምንም የማይወጣለት መሆኑን በተደጋጋሚ ሰብኳል፡፡ በአዋጁ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ትችቶችን ከማጣጣልም ቦዝኖ አያውቅም፡፡
ይህ የመንግስት አተያይ እንዳለ ሆኖ በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ ድንጋጌዎች አሉ ለማለት ወይም ስለ አዋጁ እንከን የለሽነት ለመመስከር የሰከነ የህግ ትንታኔ ያስፈልጋል፡፡ አዋጁ ይሰረዝ የሚለውን ጥያቄ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወምም እንዲሁ በአዋጁ ላይ የሚነሱትን ክርክሮች መፈተሸ ተገቢ ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከትንታኔውና ከፍተሻው በፊት አዋጁን ለከፋ ጥርጣሬ የሚዳርጉ ሦስት ገፊ ምክኒያቶች አሉ፡፡
1ኛ የጸረ ሽብር አዋጁ ላይ የሰፈረው የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር እንደሚገልጸው ህጉ ሊወጣ የቻለው “ሕዝቦች በሰላም በነጻነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያላቸው መብት ከሽብርተኝነት አደጋ ሁልጊዜ መጠበቅ ያለበት በመሆኑ” በማለት የአዋጁን አላማ ህዝባዊነት ያስረዳል፡፡
በርግጥ ይህ አዋጅ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የወጣ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ፍተሻ ከመጀመራችን በፊት ስለ አዋጁ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ስለ እንከን የለሽነቱ የሚሰብኩት መንግስትና ደጋፊዎቹ ብቻ መሆናቸውና የአዋጁን እንከኖች ከመንቀስ ጀምሮ ይሰረዝ እስከሚል ጠንካራ ውግዘት የሚያቀርቡት ደግሞ አሁን ያለውን መንግስት ባንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚቃወሙ አካላት መሆናቸው ብቻ በአዋጁ አላማ ላይ አንዳች ጥያቄ ለማንሳት የሚጋብዝ ነው፡፡
2ኛ አዋጁ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ አስራ ሰባት ጋዜጠኞችና በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና በሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ፖለቲከኞችና የፓርቲ አመራሮች የዚህ አዋጅ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የመንግስት ተቃዋሚዎችና ተቺዎች ከዚህ አዋጅ ኢላማ ውጪ ስለመሆናቸውና አዋጁ ኢላማ ያደረገው በርግጥ አሸባሪዎችን ብቻ ስለመሆኑ እንድንመረምር ይገፋፋል፡፡
3ኛ መንግስት፣ በአሸባሪነት ተከሰው ስለታሰሩ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ፖለቲከኞች ሲጠየቅ የሚመልሰው የንጹሀን ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለደህንነታቸው የታሰበላቸው ንጹኃን ዜጎች መንግስት አሸባሪ ያላቸውን እስረኞች እንዲፈታ የታሳሪዎቹን ፎቶ በመያዝ አደባባይ ወጥተው ሲጠይቁ ተስተውሏል፡፡ ይህ ወለፈንዳዊ ሁነት አመዛዛኝ ህሊና ያለውን ማንንም ሰው፣ አሸባሪ ተብለው የታሰሩት ሰዎች በርግጥ አሸባሪ ናቸው? ከሚል ጥያቄ አያስመልጥም፡፡
እነዚህ ሦስት ነጥቦች የጸረ ሽብር አዋጁን እንከን የለሽነት እንድናምን ሳይሆን አዋጁ በጥንቃቄ መፈተሸ እንዳለበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመሆኑም አንድነት ፓርቲ ይሰረዝ ያለበትን ምክኒያት በዝርዝር የማስረዳት ሀላፊነቱን ለራሱ ለአንድነት በመተው እኛ ግን በሚቀጥለው ሳምንት “የጸረ ሽብር አዋጁ ለምን ይሰረዝ?” የሚል አብይ ጥያቄ በማንሳት ፍተሻችንን እንጀምራለን፡፡
የሳምንት ሰው ይበለን
ቺርስ!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s