ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ዐረፉ፤ የቀብር ሥነ ሥርዐቱ ነገ በኢየሩሳሌም ይፈጸማል | ሐራ ዘተዋሕዶ

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ከሠላሳ ዓመታት በላይ አገልግለዋል

‹‹በጌቴ ሰማኔ፣ በጎልጎታ፣ በዴር አብርሃም ሁሉ ሰፊ ይዞታ እንዳለን በታሪክ ሰፍሯል፡፡ ግብር ለመገበር አቅም ስላነሰን ዴር አብርሃምን ግሪኮች ወሰዱብን፤ ቤተ ልሔም ያለውን ርስታችንን አርመኖች ወስደውታል፤ በዚያ ላይ ያለንን መረጃ በሙሉ ቀደም ሲል አርመንና ግብጾች ወስደው አጥፍተውታል፡፡››

‹‹ግብጾች በጣም ነው የሚከራከሩት፡፡ በዴር ሡልጣን ጉዳይ ግብጾች ያቋቋሙት ትልቅ ኮሚቴ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የእኛ ነው ካልን ዴር ሡልጣን ከእጃችን አይወጣም፡፡ ለዚህ ቦታ መርጃ የሚኾን አንዳንድ ፕሮጀክት መዘርጋት አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ ምእመናን እጃችኹን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ዴር ሡልጣን አለን ማለቱ ብቻውን በቂ አይኾንም፡፡››

‹‹ሕዝቡ ከገዳሙ ጎን ቆሞ፣ ገዳሞቻችን እንደ ሌሎቹ በልጽገው ፈጣሪ እንዲያሳየኝ ጸሎቴ ነው፡፡ የዴር ሡልጣን ክርክር ፍጻሜ አግኝቶ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መብቷ እስከ ኾነ ድረስ የኢትዮጵያ ምእመናን ለዴር ሡልጣን መርጃ እንዲኾን አስቦ እንደ ግብጾች አንድ ድርጅት አቋቁሞ ለዚያ ሒሳብ ተከፍቶ እንዳየው እመኛለኹ፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ለጋዜጠኞች የተናገሩት/
በመጻሕፍተ ሐዲሳት መምህርነታቸው፣ በጸሎትና የተባሕትዎ ሕይወታቸውና መፃዕያትን በሚናገሩበት ሀብተ ትንቢታቸው የሚታወቁት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዐታቸው ነገ፣ ጥቅምት ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከ፲፱፻፷፬ ዓ.ም. ጀምሮ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ባገለገሉበትና በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት አንዱ በኾነው በአልዓዛር ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡

በቆየባቸው ሕመምና በዕርግና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባረፉት በብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ለመገኘት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የባሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ወደ ስፍራው ማምራታቸው ታውቋል፡፡

በፊት ስማቸው አባ ላእከ ማርያም ዐሥራት በኋላ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተብለው ለማዕርገ ጵጵስና የበቁት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማትን የተመለከቱ ጉዳዮች እንዲያስፈጽሙ በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም. ከማኅበረ መነኰሳቱ ተልከው ወደ ኢትዮጵያ በሄዱበት አጋጣሚ ነው፡፡ በወቅቱ ከብፁዕነታቸው ጋራ በአጠቃላይ ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት ተሹመዋል፤ እነርሱም በቀደምት የኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች መንገድ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙትና በ፳፻፫ ዓ.ም. ያረፉት በገዳማቱ የሊቀ ጳጳሱ ረዳት ብፁዕ አቡነ አብሳዲ እንዲሁም የደቡብ አሜሪካው ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ናቸው፡፡

ከ፲፱፻፷፬ – ፲፱፻፸ ዓ.ም. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ካልዕ ጋራ አብረው ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በኤጲስ ቆጶስነት ከተሾሙ በኋላ ወደ ኬንያና ጅቡቲ አምርተው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ከኬንያና ጅቡቲ ተመልሰው የአፋር ሀ/ስብከት ጳጳስ ኾነዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ቆይታ በኋላ ለሕክምና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት አንዱ በኾነው በአልዓዛር ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ኖረዋል፡፡

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በነበራቸው ከ35 ዓመታት በላይ ቆይታ ስለ ቅድስናና የታሪክ ይዞታችን ተጠያቂ ከነበሩት አባቶች አንዱ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ ቤተ ልሔም ላይ የነበረው ይዞታችን ከግለሰቦች እጅ ተገዝቶ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እጅ ሲገባ ታላቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ መጋቢም ኾነው አገልግለዋል፡፡

አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የተወለዱት በ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ አካባቢ ነው፡፡ በልጅነታቸው በተወለዱበት ስፍራ የቃል ትምህርት፣ ንባብ፣ ግብረ ዲቁና ተምረዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s