ቃሊቲ ደርሶ መልስ (በመሀመድ ሀሰን)

Mohammed Hassen   ትመጪ እንደው እያልኩ ሌት ተቀን ናፋቂ

ሰርክ የማይታክተኝ አለሁሽ ጠባቂ፤

ፍቅር ተደግፌ ቃልኪዳን ታቅፌ

ትመጪ እንደው እያልኩ

ክፍት ነው ደጃፌ፤

አትቀርም እላለው በመላ በጥበብ

ምን ቀን እየገፋ አድሜዬን ብታለል፣

ቆፈን ቢገርፈኝም ጥበቃዬ በዝቶ

እኔ ግን እዛው ነኝ አላጎደልኩ ከቶ፤

ትመጪ እንደው፣

አለሁ እኔ

በፍቅር እንዳለው፡፡ …

እነዚህ ስንኞች የተወሰዱት ‹‹ትመጪ አንደው›› ከሚለው የሚካኤል በላይነህ ሙዚቃ ውስጥ ነው:: እኔ ይህንን ሙዚቃ ስሰማ ከገጣሚው ቴዎድሮ ፀጋዬ፣ ከዜማ ደራሲውና ከዘፋኙ ሚካኤል በላይነህ፣ እንዲሁም ከአቀናባሪው ሚካኤል ሀይሉ ቀድሞ ወደ ህሊናዬ የሚመጣው ጋዜጠኛ ስለሺ ሀጎስ ነው:: ዘፈኑ በወጣበት ቀን ስለሺ ስልክ ደውሎ ‹‹ቴዎድሮስ ፀጋዬን አመሰግንልኝ…›› ነበር ይለኝ:: በእርግጥም ስለሺን በቅርበት የሚያውቁት ሁሉ ይህ ግጥም በልኩ ስለመስፋቱ አስረግጠው ይነግሯችኋል:: ስልክ ደውለውለት የሚያውቁት ደግሞ ሁኔታው ሁሉ በደንብ ይገለፅላቸዋል:: ቃሊቲ ወርዳ የቀረችበት ሚስቱን በፅናት፣ በፍቅር፣ በቃሉ… ፀንቶ እየጠበቃት  ያለው ስለሺ ሀጎስ ሙዚቃው ከወጣበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወደ ስልኩ የደወለ ሁሉ ከወዲያኛው ጫፍ ይህንኑ የሚካኤል በላይነህ ሙዚቃ ያዳምጣል::

በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እና በጋዜጠኛ ስለሺ ሀጎስ መካከል ያለውን ፍቅር እና ዛሬ ላይ ያሉበትን ሁኔታ የተረዳ ሰው ደግሞ በሙዚቃው ግጥም ውስጥ ያሉት ቃላት ላይ ይበልጥ ይመስጣል:: ለዚህም ነው ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ በአንድ ወቅት ‹‹ትመጪ እንደው›› ሲል እራሱን የቻለ ሙሉ ፅሁፍ ያስነበበን:: ባይሆንማ ኖሮ እዚሁ ጉዳየ ላይ ብቻ በርካታ ተጨማሪ ነገሮች ባነሳሁ ነበር:: ስለሺ የዛሬው ርዕስ ጉዳዬ ብቸኛው ተጠቃሽ አይደለም፤ ከሌሎችም ጋር አብሮ የሚነሳ እንጂ:: ለማንኛውም ርዕዮት እንደምትመጣለት እኛም ተስፋ እናድርግና ወደዛሬው ጉዳዮችን እንዝለቅ::

የእናት እዳ ለልጅ

የኢህአዴግን እዳ የምዘረዝርበትን የዛሬውን ፅሁፌን እንድሞነጫጭር መነሻ የሆነኝ ሌለኛው የሚካኤል በላይነህ ሙዚቃ እንደሆነ ስጠቅስ ሚኪ እራሱ ዘፈኑ ተተርጉሞበት በአሸባሪነት እንዳይከሰስ ትሰጉ ይሆናል:: ኢህአዴግ ምን ገዶት፣ ከፈለገ ‹‹እንዲህ ያለውን ምርጥ አልበምማ ያለ አሽባሪዎች አንዳች ድጋፍ ልትሰራው አትችልም::›› ሊለውና የክስ መዝገብ ሊከፍትበት ይችላል::…መጠርጠር አይከፋም::…ስለዚህ ሁልሽም በጠርጣሪው ፓርቲ ልትጠረጠሪ እንደምትችዪ ብትጠረጥሪ ከጥርጣሬ ቀውስ ቀድሞውኑ ሊታደግሽ ይችላል::

ቅዳሜ ሰኔ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ‹‹አሸባሪ›› ወዳጆቼን ለመጠየቅ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቅራቢያ ተገኝቼ የመጠየቂያ ሰዓቱን /6:00 ሰዓት/ መድረስ እጠባበቃለሁኝ:: ሌሎች የፈትያ እና የርዕዮት ጠያቂዎችን ጨምሮ የእማዋይሽ፣ የሒሩት፣ የተፈራ፣ የሀቢባ እና የጫልቱ ጠያቂዎችም ልዩ ተጠያቂዎች የሚጠየቁበትን ስድስት ሰዓት በመጠባበቀ ላይ ናቸው:: ከመካከላችን አንዱ ስልኩን አወጣና ወደሆነ ቦታ ደወለ:: ስልኩን ጆሮወ ላይ አድርጎም፡-

      የሰማይ መሬቱ የባህር ስፋቱ

      እንዳለም ዳርቻ እንደ ‘ርቀቱ

      አይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ

      ስወድሽ ስወድሽ ውዴ ወድሻለሁ፤….

እያለ የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥም በዜማ እያዋዛ መዝፈን ያዘ::.. ወዲያውም የስልኩ ጥሪ የሆነውን የሚካኤል በላይነህን ሙዚቃ እያንጎራጎረ መሆኑን ተረዳሁ::… የደወለው ናርዶስ ጋር ነው:: ዘወትር እናቷን እማዋይሽን ለመጠየቅ ከቃሊቲ የማትጠፋው ናርዶስ ዛሬ በአቅራቢያው ስላልታየችው ነበር ይህ ሰው ስልክ የደወለው:: ናርዶስ ግን ቀድማን መጥታ ኖሮ ግቢ ውስጥ በጊዜ ገብታ ሰዓቷን እየተጠባበቀች ነው:: ስለሺ የፍቅሩን መምጣት በተስፋ ሲጠብቅ ‹‹ትመጪ እንደው…›› ሲል፣ ናርዶስ ደግሞ ‹‹ስወድሽ›› በሚል ለእናቷ ያላትን ጥልቅ ፍቅር እየገለፀች ነው::…

ኢህአዴግ ባለ እዳ ከሆነባቸው ዜጎች ውስጥ አንዷ ናርዶስ ናት:: እንኳን መከራን ፍቅርን እንኳን በአግባቡ መሸከም የማይችለው የናርዶስ ጨቅላ እድሜዋ ያለ ጊዜው መከራ እንዲያጎብጠው ሆኗል:: በወጉ እንኳን ያልጠናችው ናርዶስ በ15 አመቷ ኢህአዴግ ከእናቷ ጉያ ነጥሏት ብቻዋን ቀረች:: እናቷ እማዋይሽ ወደ እስር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጃ ስትወረወር ናርዶስ ባዶ ቤት ታቅፋ ቁጭ አለች:: ከማትችለው የእናቷ ፍቅር ተነጥላ ባዶ ቤት መልመድ አልሆንልሽ ያላት ናርዶስ ባዶው ቤት የመኖር ዋስትናዋን እንኳን ማረጋገጥ ተሳናት:: በልማት ስም አካባቢያቸወ ፈርሶ ለሁሉም ተለዋጭ ቦታ እና ቤት ሲሰጣቸው ናርዶስ ግን ሰሚ አጣች:: ከእናት አልባነት ወደ ቤት አልባነት ተሸጋገረች:: መከራ ጓዙን ጠቅልሎ የሰፈረባት ትንሿ ናርዶስ ክፉኛ ተረታች:: በአክስቷ ጎትጓችነትና አለሁሽ ባይነት ለትምህርት ወደጅጅጋ አቅንታ አክስቷን ተጠጋች::

ናርዶስ ከጥቂት ግዚያት ቆይታ ቦሀላ የእናቷ ፍቅር ጠራትና ስትበር መጣች:: ትምህርቷን ወደ አዲስ አበባ ለማዛወር ብትሞክርም እሺ የሚላት አጣች:: ዛሬ ናርዶስ አምሳያ ለሌለው የእናቷ ፍቅር ሁሉን ነገር መስዋት አድርጋ ቃሊት ትመላለሳለች:: እኩዮቿ አምረው፣ደምቀውና አጊጠው በሚዝናኑበት ወቅት፣ እሷ እዚህ ሁሉ ነገሯን ለእናቷ ሰጥታ ስለ እናቷ ትኖራለች:: ለእናቷ ሰትል የማትከፍለው አንዳች መስዋትነት የለም::…

አሁን ናርዶስና እናቷ ከሽቦው አጥር ወዲያና ወዲህ ሆነው ሰላምታ እየተለዋወጡ ነው:: እናት በሽቦው ውስጥ ሶስት ጣቶቿን አሾልካ ወደ ልጇ ላከች:: ልጅም ተንጠራርታ የናቷን ጣቶች መሳም:: በተመሳሳይ እናትም በሽቦው ውስጥ ሾልከው ያገኘቻቸውን የልጇን ጣቶች ሳመቻቸው::

ሚካኤልም ማጀቡን ቀጠለ፡-

እንደ ጽጌሬዳ

እንደ አደይ አበባ

እንደ ከርቤ ብርጉድ

እንደ ሎሚ ሽታ

አበባ እንዳየ ንብ

እኔ እወድሻለው

ፍቅርሽን በፍቅሬ

በፍቅርሽ ልቅመሰው፤…

… ልጅ በፍጥነት እናቷን ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ፀጉሯ ቃኘቻትና ‹‹ለምንድነው ፀጉርሽን ያልተሰራሽው?›› ስትል በፍቅር ተቆጣች:: እናትም ‹‹ተሰርቻለው እኮ…›› አለች::… ‹‹ያመጣሁልሽን ቀለምስ ለምንድነው ያልተቀባሽው?…›› ናርዶስ እናቷን እንደማኩረፍ ቃጣት:: እናቷ እንደምትፈልገው አልተዋበችላትም፡፡… ይሄኔ አይኔን ወደ ሁለቱም ፀጉር ላይ አሳረፍኩት:: የእናት ፀጉር በወጉ የተያዘና ለኔ እይታ ብዙም ያልከበደኝ ሲሆን፣ የልጅት /ናርዶስ/ ፀጉረ ግን ተንጨባሯል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁሉ ነገሯን ለእናቷ በማድረግ እራሷን እያፈዘዘችው መጥታለች::…

ጡት እንዳየ ህጻን

ወተት እንዳማረው፤

ጠጋ በይ ዘመዴ

አፍሽ ህይወቴ ነው፤

አፈር መሬት ትቢያ እንደሚበላው

ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፤…

ይህቺ 20 ዓመት እንኳን በወጉ ያልሞላት ታዳጊ ምን በወጣት ነው ይህንን ሁሉ እዳ /ፍዳ ብለው ይሻላል/ የምትከፍለው? ኢህአዴግስ ቢሆን የዚህችን ልጅ እዳ እንዴት ቢያደርግ ነው ከፍሎ የሚጨርሰው? ቢገደል፣ ቢታሰር፣ ቢሰቀል፣…? እንዴት ይህ የናርዶስን እዳ ይመልሳል? በስርዓቱ ተጠያቂ ሆኖ እዳ ከፋዩስ ማን ነው? እውነት እንዲህ ያለው በደል በፍ/ቤት አልያም በባህላዊ የሽምግልና ስርዓት እንኳን ሊካስ፣ ተመጣጣኝ ፍትህ ሊያገኝ ይችላል? እንጃ እኔ ግን አይመስለኝም፡፡

በፅሁፌ መግቢያ ላይ ያነሳሁት ተስፈኛው ስለሺ (ዛሬ እንኳን ጭራሽ እንዳያገኛት ተደርጓል) ሌላኛው ፍዳ ቀማሽ ሆኖ ከናርዶስ አጠገብ ቆሞ ከፍቅሩ ርዕዮት ጋር በስስት እየተያዩ ያወራሉ:: ከተመደበላቸው ሰዓት ጋርም እሽቅድድም የያዙ ይመስል፣ አንድ ሰኮንድ እንኳን ለአይናቸው እርግብግቢት በመፍቀድ ማባከን የፈለጉ አይመስሉም:: ‹‹የፍቅር አምላክ ይሄኔ ምን ይሰማው ይሆን?›› ስል አሰብኩኝ፡፡… ያፈቀሩትን ሰው በሽቦ ፍርግርግ ውስጥ አድርጎ እንቁልልጭ ማለት ምህረት ያሰጥ እንደሆን እርግጠኛ አይደለሁም::… ስለሺ ስለ ፍቅሩ ብዙ ተሰቃይቷል::… ቤተሰቦቿ ተንከራተዋል::… እና ኢህአዴግ ለስለሺ ምን ቢያደርግ ነው ፍቅሩን፣ ልቡን፣ ግዜውን፣ ውበቱን፣ ሰውነቱን፣ ጉልበቱን፣ ስራውን… መልሶ ሊከፍለው የሚችለው? ምንስ የሞራል ብቃትና አቅም ይኖረዋል? ስለዚህ ኢህአዴግ በምንም መንገድ ከፍሎ የማይጨርሰው ፍዳ /እዳ/ ባለቤት ነው:: ስለሺ ግን አሁንም ዕናቱን፣ ተስፋውን እና ናፍቆቱን በልኩ በተስፋው ዜማ በኩል ሲገልፅ ይሰማኛል:-

      … በናፍቆትሽ እሳት ነድጄ ሳልከሰም

      ባይንሽ በጠረንሽ መልሼ እንዳገግም፤

      ሳዜም እኖራለሁ ፀሎት ስደጋግም

      ካለሁበት ድረስ እግርሽ እንዲረዝም፤

      ልምጣ ያልሽ እንደሆን ቀና ነው ጎዳና

      ልቤ ተመላልሶ ደልድሎታልና፤

      ምኞት የማይደክመው ልቤ ልበ ብርቱ

      ትዝታም አይደለ ተስፋ ነው ቅኝቱ፡፡ …

ትላንትን ብቻ በትዝታ እያላመጠ ለመኖር ሳይሆን፣ ነገንም በተስፋ ይጠብቃታል:: ፍቅሯን ጨምሮ ቤተሰቦቿ ያዩት ፍዳ ስለመከፈሉ እንጃ እንጂ፣ ተስፋቸውስ በከንቱ የሚቀር አይደለም::…

 

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s