ከብአዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ከአቶ አለምነው መኮንን ጋር የተደረገ ሙሉ ቃለ ምልልስ /ኢዜአ/

ባህርዳርImage የካቲት 15/2006 ከ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አለምነው መኮንን ከጋዜጠኞች ጋር የካሄዱት ቃለ ምልልስ ሙሉ ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ጥያቄ፤- በቅርቡ እርሰዎ በመሩት የስልጠና መድረክ የአማራን ህዝብ ዝቅ የሚያደርጉ አገላለጾች ተሰንዝሯል በሚል አንዳንድ ወገኖች ጥያቄ ያነሳሉ። ለመሆኑ የስልጠናው ተሳታፊዎች ማንነት፣ የስልጠናው ርዕሰ ጉዳይና ዋና ዋና ጭብጦች  ምን ምን ነበሩ?

አቶ አለምነው፤- እንደሚታወቀው የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ዘርፈ ብዙ የማስፋፊያና የለውጥ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው።የሚዲያ አውታሮችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በድርጅቱ ያለውን የሰው ሃይል አቅም መገንባት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በቅርቡም ለ20 ቀናት በሁለት ዙር የሙያተኞችና አመራሮችን አቅም ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱ ይታወቃል። በአንድ ዙር ከ100 የሚበልጡ ሰልጣኞች የተሳተፉበት ነው። የስልጠና መድረኩ ከክልሉ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ሙያተኞችና አመራሮች ላይ ነው።

የተነሱ ርዕሰ ጉዳዮችም በመንግስት ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና በልማታዊ ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮረ ሲሆን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዳዮች፣ የገጠር ልማት ስትራቴጂ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰነድና የልማታዊ ጋዜጠኝነት በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

በዚህም እኔ ስልጠና እንድሰጥ የደረሰኝ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዳዮች የሚለው ሰነድ ላይ ነው። በክልሉ መንግስት ተነሳሽነት ጋዜጠኞቹን በማሰልጠን በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ሙያተኞች እንዲሆኑ የሚያስችል ስልጠና ነው።

በክልሉ አብዛኛው ህዝብ የሚኖረው በገጠሩ ክፍል ነው። ይህን ህዝብ በማደራጀት አዳዲስ ቴክኖሎጅና አሰራሮችን በመተግበር ምርታማነትን ማሳደግ የመንግስት አቅጣጫ ነው። በዚህም የመረጃ ቅብብሎሽን በማጠናከር የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት በማቀላጠፍ የጋዜጠኛው ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ስለተማነበት ስልጠናው የተካሄደው።

እንደሚታወቀው የዴሞክራሲ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሚለው ሰነድ ሁልጊዜም መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተያይዞ በስልጠናዎች ሁሉ መጀመሪያ ላይ የሚሰጥ ነው። ሰነዱ ለአብዛኛዎቹ ባለሙያዎች አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተሳታፊዎች የፈለጉትንና የመሰላቸውን ሃሳብ በነጻነት እያነሱ እንዲወያዩ፣ እንዲከራከሩና በሁለትዮሽ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተካሄደ መድረክ  ነበር። በመጨረሻም ገዥ በሆነው ሃሳብ ላይ መግባባት እንዲደርሱ ለማድረግ መድረኩ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ተደርጎ የተመራ ነበር።

በዚህም የብሄር ብሄረሰብ እኩልነት እስከ መገንጠል የሚለው መርህ ባለፉት 23 ዓመታት ብሄር ብሄረሰቦች አርስ በእርሳቸው ተቀራርበው ጠንካራ አንድነት መመስረት መቻላቸው የተገለጸበት ነው። የጾታ፣ የሃይማኖት እኩልነት መከበሩ ለሁሉም ህዝብ እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አድል የሰጠ በመሆኑ ክልላችንም ሆነ አገራችን አሁን ላስመዘገቡት ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት መሆኑም ተነግሯል። በጋዜጠኞቹ በኩልም በነበራቸው ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት የተነሳ እኛም ሳንሰስት እነሱም ሳይደብቁ በሁለትዮሽ የሃሳብ ቅብብሎሽና በገዥ ሃሳብ ላይ መግባባት ነበር።

ሰልጣኞቹ አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በብሄረሰብ እኩልነቶች፣ በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ በጾታና በሃይማኖት እኩልነቶች፣ በመሬትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በርካታ ወጣ ያሉ ሃሳቦች ተነስተዋል።

በኛ በኩልም በእኔ ሁኔታም ቢሆን በሌሎች መድረኮች እንደምናደርገው ትክክለኛ ሃሳቦችን እናደንቃለን የተሳሳቱትን ነቅፈን በትክክለኛው ሃሳብ እንዲተካ መርሆዎቻችን ላይና ሰነዶቻችን ላይ የተኮረ ገለጻ እናደርጋለን። እኔም ያደረኩት ይሄን ነው።

በዚህም አሁን ባለው ሁኔታ በአገራችን ያሉ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች አቅም በእኩል በማሳተፍ የአገራችን እድገት ከማፋጠን አኳያ ያለውን አደጋ ነግረናቸዋል። እነሱም በማንበብና በመጠየቅ ሂደት ተጋግባብተን ነው የተለያየነው።

የስልጠናው ዓላማም እንደሁልጊዜው የድርጅቱ መድረክ ሁሉ ትክክል የሆኑትን ሃሳቦች በማድነቅና ይበልጥ ግንዛቤ እንዲያዝባቸው በማድረግ፣ እንዲሁም የተነሱ የተሳሳቱ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት በማካሄድና ስህተትን በማሳየት ታርመው በትክክለኛው ሃስብ እንዲተኩ የማድረግ ስለነበር የኔ ማብራሪያም በመረዳዳት ላይ  ያተኮረ ነበር።

ጥያቄ፤- በዚህ ስልጠና ላይ ለጥያቄ መነሻ የሆነውና አነጋጋሪ ነው ተብሎ የተነሳው  ጉዳይ ምንድን ነው? በስልጠናው ሂደትስ ከሰልጣኞች ጋር የተፈጠረ አለመግባባት ነበር ወይ?

አቶ አለምነው፤- በስልጠናው ሂደት ባለፉት 23 ዓመታት በተፈጠሩ የተለያዩ መድረኮች ሲነሱ ከነበሩ ሃሳቦች የተለየ አልተነሳም። ይህም ማለት በሌሎች መድረኮች እንደሚነሱት ሁሉ በብሄር እኩልነትን የሚቃወሙ ሃሳቦች በሰፊው ተንጸባርቀዋል። ለምሳሌ ሌላው ብሄር ተጠቃሚ እየሆነ ሲመጣ የኛ ብሄር እየተጎዳ ነው የሚልና ከሃይማኖት፣ ጾታ እኩልነቶች ጋር ተያይዞ የተሳሳተ ሃሳቦች ተነስተዋል።

በእኔ በኩል የተገለጹ ሃሳቦች- ለተነሱ ሃሳቦች ማብራሪያ ስሰጥ የብአዴንና የኢህአዴግንና የመንግስት  አቋም የሚገልጽ ነው። ውይይት የምናደርገው የፖሊሲ ሰነዱ መሰረታዊ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ በመሆኑ። የውይይቱን ሂደትም ነጻ ለማድረግ በመታሰቡ ቀረጻ የለውም።

በተቃዋሚዎች አለ ተብሎ የሰማሁት ሃሳብን እኔ አላልኩም። እንዴትስ ልል እችላለሁ? አንደኛ ነገር ለህዝብ ከብር አለኝ። ህዝቦች እንዲለሙና እንዲጠቀሙ ሌት ከቀን የምሰራ ሰው ነው ነኝ። እኔ ማን ምን ሁኜ ነው የወጣሁበትን ብሄር ዝቅ የሚያደርግ ሃሳብ የምናገረው። እኔም እኮ የህዝብ ክብር ያለኝ ሰው ነኝ። ድርጅታችም ከምንም በላይ በላይ የሚሰራው ለህዝብ ክብር ነው። ለህዝብ ክብር ቅድሚያ የሚሰጥ ድርጅት ነው። የእኔ ግላዊ ባህሪም ለህዝብ ክብር ቅድሚያ የምሰጥ ሰው ነኝ። ስለዚህ አልክ የተባልኩት ሃሳብ መሰረተ ቢስ ክስ ነው።

እኔ ማንና ምን ስለሆንኩ ነው የተወለድኩበትን፣ ያደኩበትንና የወጣሁበትን ማህበረሰብ ላንቋሽሽ የምችለው? እንዴትስ ሊገመት ይችላል?

ይህ ድርጊት በተቃዋሚዎች በቆርጦ ቀጥል የኮምፒውተር ዘዴ የተቀነባበረ ሴራ ነው።  ተቃዋሚዎች እኛን ከህዝብ ለመነጠል የሚያደርጉት ሴራ ነው። በነገራችን ላይ ይህ የተቃዋሚዎች አካሄድ የቆየ ተግባር  ነው። በቀጣይም ይቀጥላል።

አሁንም እኔ ለክልሉ ህዝብ ላረጋግጥ የምፈልገው ያውም የራሴን ብሄር ዝቅ የሚያደርግ አንድም ሃሳብ አልገለጽኩም።

ይሁን እንጂ የብሄር እኩልነት ላይ አንዱን ብሄር ከፍ አንዱን ዝቅ አድርጎ የማየት አስተሳሰቦች ስለተነሱ እኔም አንዱን ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ… ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግ ከቀድሞ ገዥዎቻችን የወረስነው የትምክህት አመለካከት በመሆኑ መወገድ አለበት ብያለሁ። አሁን ከተፈጠረው ብሄርና ብሄረሰቦች እርስ በእርስ በመፈቃቀር ጠንካራ አገራዊ አንድነት ግንባታ ታላቅ አደጋ መሆኑን በመግለጽ መታረም እንደሚገባ ገልጫለሁ።

እንደሚታወቀው ብአዴንም ሆነ ኢህአዴግ ትምክህትና ጠባብነት የአገራችንን ጠንካራ አንድነት ለማስቀጠል አደጋ መሆኑን በመለየት ሁለቱንም ለማስተካከል በመታገል ላይ ነን ።

እንደ ብአዴን የምንታገለው በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተው ጠንካራ የህዝብ አንድነት በአጉል አስተሳሰብ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ትናንትም ዛሬም የትምክህት አስተሳሰብን ለማስተካከል እየታገልን እንገኛለን።

ከቀድሞ ገዥዎች የወረስነው የትምክህት አስተሳሰብና አመለካከት ለዘመናት የኛን ብሄር ሲጎዳ የነበረ ነው። በህገ መንግስቱና በፌደራላዊ ስርዓቱ መሰረት በህዝቦች መፈቃቀር የተመሰረተውን እንደ ብረት የጠነከረ አንድነት ይጎዳል። እኛ ብአዴኖች አንዱን ብሄር ከፍ የሚያደርግ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግ ሃሳብን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ እንታገላለን።

ስለዚህ በእኔ በኩል የሞገትኩት ትምክህት የክልሉን ህዝብ መብትና ጥቅም እንደሚጎዳ ነው። ምክንያቱም ትምክህት ለኣማራ ህዝብ መቼም ቢሆን ጠቅሞን አያውቅም የሚለው ላይ በማተኮር ነው።

ይህ ከሆነ ለምንድን ነው በተቃዋሚዎች በኩል በኮምፒውተር ተቀነባብሮ አየር ማዋል ያስፈለገው ? የሚለው በቂ መልስ ማግኘት አለበት።

እንደ ገለጽኩት ለእኔ የተሰጠኝ የአራት ቀናት ስልጠና ነበር። በአራት ቀናት ውስጥ የተናገርኳቸውን ቃላቶች በመምረጥና በማዳቀል በተዛባ አኳኋን ለምንድን ነው ህዝቡን ለማደናገር የሞከሩት ሲባል በኔ ግምት ሶስት ምክንያቶች አሉ።

አንደኛው የብአዴን አመራሮች የድርጅታቸውን ፖሊሲዎች መርሆዎች ለህዝቡ እንዲያሳውቁና ህዝቡ እውነቱን እንዲጨብጥ ካለመፈለግ የመነጨ ነው። እኛና ተቃዋሚዎች ባለን መሰረታዊ ልዩነቶች ተቃዋሚዎች መሰረታዊ ልዩነቶቻችን ባደባባይ እንዲገለጹ፣ ህዝብ እንዲያውቀውና ፍርዱን እንዲሰጥ አይፈልጉም።

እንደሚታወቀው በብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት፣ በመሬት፣ በጸታና በሃይማኖት እኩልነትና ሌሎች ጉዳዮች ግልጽ የሆነ ልዩነት አለን። ስለዚህ በልዩነቶቻችን ላይ የድርጅታችንን መርህ እንዳንገልጽ ይፈልጋሉ። ልዩነታችንን ህዝቡ እያወቀና እየተገለጸ ከሄደ የነሱ ተቀባይነት እየቀነሰ ይሄዳል።

ስለዚህ እኛንና የእኛ ጓዶች በሚካሄዱ ስልጠናዎችም ሆነ መድረኮች በቆርጦ ቀጥል የኮምፒውተር ቅንብር ስማችን ይጠፋል በሚል እውነቱንና ያመንበትን እንዳንናገር ለማድረግ የተደረገ ሙከራ ነው።

እኛም እንዳንናገር፣ ህዝቡም ትክክለኛ እውነቱን እንዳያውቅና ትክክለኛ መረጃ እንዳይኖረው ያለመ ነው። ዛሬ የመረጃ ዘመን ነው። ህዝባችን ተገቢውን መረጃ እንዳያገኝ እኛ የተናገረውን ከነሙሉ ቁመናው እንዳይቀርብ አዛብቶ በማቅረብ የብአዴን አስተሳሰብ በህዝብ ዘንድ እንዳይሰርጽ የተደረገ ጥረት ነው።

ይህ ላለፉት 23 ዓመታት ተሞክሮ አልተሳካም በቀጣይም የሚሳካ አይመስለኝም። ምክንያቱም አካሄዱ ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ እውነቱ ጸሀይ ሲወጣና እያደር ሲሄድ ስለሚገለጥ።

ሁለተኛው በቆርጦ ቀጥል የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ለማምታት የሚሞክሩት ህዝቡ የማመዛዘን ችሎታው ዝቅተኛ ነው ብለው ከማሰባቸው የተነሳ ነው። ትናንት ዛሬ አይደለም ህዝቡን በማደናገር ለፈለጉት ዓላማ የሚያሰልፉበት ጊዜ አይደለም። የብአዴን ትክክለኛ ስእል ለህዝቡ እንዳይደርስ የሚደረግ ሙከራ ነው።

እውነቱ ግን የክልላችን ህዝብ በማታለልና በማጭበርበር ለፈለጉት ዓላማ የሚያሰልፉት ሳይሆን የማመዛዘን አቅሙ ያደገ በመሆኑ ግራና ቀኙን ሰምቶ ለማመዛዘን ትዕግስት የተላበሰ ነው።

አሁንም በተጨባጭ የታየውም ይሄው ነው።ህብረተሰቡ እያለ ያለው እንዴት የኛ ተወላጅ የራሱን ብሄርና ራሱን ሊወቅስ የሚችል ሃሳብ ይሰነዝራል የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው።ይህ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታው የዳበረ ህብረተሰብ ለመሆኑ ማሳያ ነው። እነሱም ህዝቡ ላነሳው ለዚህ ጥያቄ መልስ ያዘጋጁ አይመስለኝም።

ሶስተኛው ምክንያት በአገራችንና በህዝባችን ችግሮችና የመፍትሄ ቀመሮቻችን ላይ ብአዴን/ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ሰፊ ልዩነት አለን። በእኛና ተቃዋሚዎች መካከል ከፍተኛ ልዩነት በመኖሩ በየጊዜው በህዝብ እውነተኛ ዳኝነት ነው ከዚህ የደረሰ ነው።

ልዩነቶችንም በብሄር ብሄረሰቦች መብትና ተከባብሮ መኖር፣ የግልና የቡድን መብቶች ላይ እኛ የሀገራችን ህዝቦች አንድነትን ለማስቀጠል በመካበበር ላይ የተመሰረተ ሆኖ እንዲዘልቅ የግልና ቡድን መብቶች መከበር አለባቸው ስንል እነሱ ግን የግለሰብ መብት ከተከበረ በቃ ይሉናል።

በኛ በኩል የአማራና የሌሎች ክልል ህዝቦች በፌደራላዊ ስርዓቱ የግልና የቡድን መብቶች መከባበር በህዝቦች መከባበር የተጠናከረ አንድነት መገንባት ችለዋል ስንል ተቃዋሚዎች የብሄር እኩልነትን አይቀበሉም።

በህዝቦች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ላይም ብአዴን ኢህአዴግ በየደረጃው የሚገኘው ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት መዘርጋት አለብን ብለን ስንረባረብ እነሱ በጥቂት ሃብታሞች ለውጥ ይመጣል ይሉናል። በሃይማኖትና በጾታ እኩልነትም እንደዚሁ።

በመሬት ጥያቄ ላይም መሬት የመንግስትና የህዝብ ሃብት ነው ። መሸጥ መለወጥ የለበትም። ሀገራችን አሁን ለተያያዘችው ፈጣን ልማት ወሳኝ መሳሪያ ነው ስንል መሬት መሸጥ መለወጥ አለበት ይላሉ።

እንዚህንና ሌሎች ልዩነቶቻችን ትናንትም ዛሬም ሆነ ነገ እኛንና እነሱን ሊያግባቡን አይችሉም። በህዝብ ዳኝነት ብቻ እውነተኛ ፍትህ ማግኘት የሚቻለው።

ስለዚህ ምርጫ በመጣ ቁጥር እንደ ሌሎች አገሮች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የፖሊሲ አማራጮችን በማቅረብ ተከራክረው የህዝብ አመኔታን ከማትረፍ ይልቅ ድርጅታችንና  አመራሮችን የማጥላላት ተግባርን ነው የሚመርጡት።

በኛ በኩል ህዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ በመጣ ቁጥር በቆርጦ ቀጥል የኮምፒውተር ዘዴ የሚያደርጉትን ማደናገር እንዳይቀበል መልዕክት ማስተላለፍና ማሳወቅ ነው የሚጠበቅብን።ይሄንም በየጊዜው እያደረግን ነው የምንገኘው።

ጥያቄ፤- ጉዳዩ ይህ ከሆነ ታዲያ አንዳንድ ወገኖች በተለይም ተቃዋሚ ሃይሎች ጉዳዩ የአማራ ህዝብ ማንነት ዝቅ የደረገ ነው ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? መነሻቸውስ ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ አለምነው፤- መነሻቸው ቀደም ሲል ከጠቅስኳቸው በተጨማሪ አሁን ያለንበት ወቅት የምርጫ ዋዜማ ላይ ነው። ታስታውሱ ከሆነ በ2002 ምርጫ ዋዜማ ዋዜማ የሱዳን ድንበር ጉዳይ ተነስቶ የክልሉ አመራሮች ስም ሲብጠለጠል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የተከበሩ መለስ ዜናዊ ሳይቀር በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንዲሰጡ የተደረገበት ወቅት ነበር።

አሁንም የምርጫ ዋዜማ ሲመጣ ተረስቶ የኖረው የድንበር ጉዳይ ተነስቶ የክልላችን ፕሬዜዳንት መግላጫ እንዲሰጡ ተደርጓል። ነገሩን ባለማቆም የክልል አመራሮቻችንን የማጥላላት ዘመቻ ተጀምሯል። ምርጫ ሲቀርብ በሌላው ዓለም የፖሊሲ አማራጮችን ይዞ በመቅረብ የህዝብን ይሁንታ ለማግኘት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ክርክርና ውይይት ይካሄዳል።

በኛ ሀገር ያሉ ተቃዋሚዎች ደግሞ ገና ቁመናቸው ያልተስተካከለ በመሆኑ እኛ ብአዴኖችና ኢህአዴጎች እንዳንናገር፣ ተናግረንም እውነቱን ህዝብ እንዳያውቀው ከማድረግና በእውነት መረጃ ላይ ተመስርቶ ትክክለኛ ፍርድ እንዳይሰጥ የመከልከልና የማጥላላት ዘመቻ ነው ቀድሞ የሚሰራው።

ይህ አካሄድ የአገራችን ዴሞክራሲ አያሳድገውም። ለክልላችን ልማትም የሚጠቅም አይደለም። እኔ እንደሚመስለኝ ይህ አካሄድ የሚያስኬድ አይደለም።ተገቢም ነው ብየ አላምንም። ዋናው ጉዳይ አማራጭ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ መቅረብና በመድረክ መታገልና የህዝብን ይሁንታ መጠየቅ ነው።

በጣም የሚገርመኝ የብአዴን/ ኤህአዴግ አመራሮችና አባላት የህዝቡ ኑሮ ሲለወጥ የኔም ህይወት በሂደት ይለወጣል ብለው ውሏቸውና አዳራቸውን ከአርሶ አደሩና ልማት ካለበት ቦታ ሁሉ በማድረግ እየደከሙ እና እየታተሩ  በሚገኙበት ወቅት ስማቸውን በቆርጦ ቀጥል የኮምፒውተር ቅንብር በሌሎች መንገዶች ማብጠልጠል ተገቢ አይደለም። በኔ በኩል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከእንደዚህ ዓይነት የማደናገር ድርጊት እንዲቆጠቡ ነው መልዕክት የማስተላልፈው።

ጥያቄ፤- ወደሌ ሌላ ጥያቄ ላምራና ብአዴን/ ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ እንደመሆኑ የክልሉን ህዝብ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ መስመር በጽናት በመምራትና በማስተዳደር ረገድ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? እየተመዘገቡ ያሉ ዋና ዋና ውጤቶችን ቢያብራሩልን?

በዓለም ደረጃ ህዝብ የማስተዳደር ብቃት ያለው ድርጅት ነው ተብሎ ሊፈረጅባቸው የሚችል አራት አውራ መስፈርቶች አሉ።

እነዚህ አውራ መስፈርቶችም 1. በሀገሩ ወይም በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን መቻል። 2. ብሄራዊ አንድነትን እያጠናከረ የመሄድ ችሎታ። 3. የህዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢን በዘላቂነት እያሳደጉ የመሄድ ጉዳይ። 4. የምርት ሃይሎች የሚባሉትን ማለትም ጉልበት፣ መሬትና የአካባቢ ጸጋዎችን ምርታማናት በዘላቂነት የማሳደግ ጉዳይ ናቸው።

በእነዚህ አራት ጉዳዮች ድርጅታችንን ስንመዝነው በቀጣይ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣ ድርጅት ነው። በእያንዳንዱ ጉዳይ ስናየውም ብአዴን ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የአማራ ክልል በሰላምና መረጋጋት በኩል ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም የሰፈነበት ክልል መሆኑን ህዝቡ በሙሉ ልብ መመስከር የሚችለው ጉዳይ ነው።

አንደኛ ብሄራዊ አንድነትን በዘላቂነት ከማጠናከር አኳያም ለዚህ መሰረቱ በህዝቦች መፈቃቀር የተመሰረተው ህገ መንግስታዊ ስርዓትና ከዚህ የሚመነጨው በህዝቡች እኩልነት፣ሙሉ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የተዘረጋው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአገራችን ይበልጥ እየዳበረ መሄዱን ማየት ይቻላል። ህገ መንግስቱን ከማርቀቅ ጀምሮ የፌደራላዊ ስርዓቱ እንዲዳብር በማድረግ  የብአዴን/ ኢህአዴግ አመራሮች የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መምጣታቸው እውን ነው።

ሁለተኛ ከህዝብ ነፍስ ወከፍ ገቢ አንጻር 87 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ነዋሪ አርሶ አደር ነው። ቀሪው 13 በመቶ ደግሞ የከተማ ነዋሪ ነው። አብዛሃኛው ህዝብ የገጠር ነዋሪ ከሆነ ይነስም ይብዛም መሬት አለው ማለት ነው።

አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው። ስለዚህ አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ድርጅታችን ገጠሩን ማዕከል ያደረገ ስራ ሰርቷል። በተሰራው ስራም አበረታች ለውጥ መጥቷል።

ይህን ለማረጋገጠጥ በ1985 የክልሉ ጠቅላላ ዓመታዊ የሰብል ምርት 28 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነበር። የህዝብ ቁጥሩም በአንጻሩ እንዲሆ ያደገ አልነበረም።

በዚህም የክልሉ የነፍስ ወከፍ ገቢ የነበረው ሁለት ኩንታል ብቻ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የማዕከላዊ እስታቲስቲክስ መረጃ እንዳረጋገጠው የክልሉ አጠቃላይ የሰብል ምርት ከ91 ሚሊየን ኩንታል በላይ አድጓል።  የነፍስ ወከፍ ገቢውም የመስኖ ልማትን ጨምሮ ወደ አምስት ኩንታል ማሳደግ ተችሏል።

ሶስተኛ የምርት ሃይሎችን ምርታማነት በማሳደግ በኩልም ጉልበት፣ መሬትና የአካባቢ ተሰጥኦን በማበልጸግ ርብርብ እየተደረገ ነው። በሰው ሃይል ልማት ሀገራችንም ሆነች ክልሉ ከፍተኛ እምርታ በማስመዝገብ ላይ ናቸው።

ያለውን የጉልበት ምርታማነት ለማሻሻል በእውቀት የበለጸገ፣ አምራች ዜጋ ለመፍጠር ርብርብ እየተደረገ ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጅ የሚጠቀም ሃይል በመገንባት የተገኘው ለውጥም ቀላል የሚባል አይደለም።

በዚህም  በአማራ ክልል ብቻ ከ4 ሚሊየን በላይ የሚሆን ህዝብ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የሰው እውቀት፣ ጉልበትና ጭንቅላት እየለማ ከመሆኑም በላይ ለአገራዊ እድገቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል።

በመሬት በኩል ለዘመናት በደን መጨፍጨፍ፣ በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴና ሌሎች ምክንያቶች የተራቆቱ ተራሮች ላይ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በማከናወን የመሬትን ምርትና ምርታማነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ በህዝቡ ሙሉ ነጻ ተሳትፎ እየተተገበረ ይገኛል።

ይህ በቀጣይ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተፈሳሶች ላይ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫውን ተከትሎ በእንስሳት፣ በመኖ፣ በንብ ማነብና ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም እንዲሰማሩ የሚያስችል ነው። ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።

ስለዚህ በእነዚህ አራት መስፈርቶች ብአዴን/ ኢህአዴግ ያለበትን ሁኔታ ስንገመግመው ህዝብን የማስተዳደርና የመምራት ብቃቱ እየደገ የመጣ ቢሆንም ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮችም አንዳሉ መገንዘብ ይገባል።

ድርጅታችን ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ያምናል። በተለይም መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ፣ በሴቶችና ወጣቶች እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያሉትን ለይቶ ችግሮችን በአጭርና በረጅም ጊዜ ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ህብረተሰቡ በየጊዜው አዳዲስ ለውጥ ይፈልጋል፤ በዚህ ረገድ የህብረተሰቡን የመለወጥ ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት የመስጠት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

በዚህም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት አቅጣጫ ሲያስቀምጥ ከልማት ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደግሞ በረጅም ጊዜ እንደየቅደም ተከተላቸው ለመፍታት እየሰራ ነው።

ለዚህም ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመስራት በአጭር ጊዜም ሆነ በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ያለ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል።

በመጨረሻ፤-  ለመላው የክልሉ ህዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ?

ለመላ የክልላችን ህዝብ የማስተላልፈው መልዕክት በአሁኑ ወቅት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብሩ አራተኛ ዓመት ላይ እንገኛለን። ይህ ዓመትም ባለፉት ሁለት ዓመታት አቅደን ነገር ግን ያልፈጸምናቸውን በዚህ ዓመት ለመፈጸም ተጨማሪ የተለጠጠ እቅድ ይዘን እየተረባረብን ነው።

የግምሽ ዓመት ግምገማችንም በዚህ ረገድ በሁሉም የልማት ዘርፎች አበረታች ለውጥ ማስመዝገብ መቻላችን ተረጋግጧል። በተፈጥሮ ሃብት፣ በእንስሳት፣ በመስኖ፣ በንብ ማነብና ሌሎች ተያያዠ ዘርፎች አረንጓዴ ኢንተርፕራይዞች ለማቋቋም እየሰራን ነው።

በከተማም ጥቃቅንና አነስተኛን መሰረት በማድረግ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል ነው። በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች ማህበራዊ ልማቶችም የተጀመረውን ስራ ህዝቡ አጣናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

የክልሉ ህዝብም ለብአዴን በምርጫ በሰጠው ኮንትራት መሰረት የሚጠበቀውን ልማትና የመልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ ደፋ ቀና እያልን እንገኛለን። በዚህም በተቃዋሚዎች አሉባልታና የተለመደ ወሬ ሳይዘናጋ የተጀመሩ የልማት ውጥኖችን ዳር ለማድረስ ከድርጅቱ ጎን መቆም አለበት እላለሁ።

አሁን እየተካሄደ በሚገኘው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በንቃት በመሳተፍ፣ ጎን ለጎን የመስኖ ልማትን ባመካሄድ፣ በከተማ ያለውም በኢንቨስትመንት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ በመሳተፍ ገቢውን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s