የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) የፓናል ውይይት – reporter

ሁለት ፅንፎች ላይ የቆመው የጋዜጠኝነት ሙያ

reporter

ከአምስት ወራት በፊት በአስታራ ሆቴል የመመሥረቻ ስብሰባውን ያካሄደውና በምሥረታ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ባለፈው እሑድ ሰኔ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ ቪው ሆቴል የፓናል ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህ ‹‹ፕሬስ፣ ነፃነት የጋዜጠኞች ደኅንነትና ልማት›› በሚል ርዕስ ሥር የተካሄደ ሲሆን፣ በዕለቱም ለመወያያ የሚሆኑ ሁለት ጽሑፎች ቀርበው ነበር፡፡

በዕለቱ ለመወያያ የሚሆኑ ጽሑፎችን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይና የሕግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ ነበሩ፡፡ ውይይቶቹን በአወያይነት የመሩት ደግሞ ጋዜጠኞቹ ኤልያስ ገብሩና አያሌው አስረስ ናቸው፡፡

እንደ ፕሮግራሙ አዘጋጆች ገለጻ በፕሮግራሙ ላይ እንዲሳተፉ ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ለሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ጥሪ ተደርጐላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ሁለቱም በፕሮግራሙ ላይ አልተገኙም፡፡

ይህ የጋዜጠኞች መድረክ በምሥረታ ላይ ያለና በቅርብ ጊዜም ሕጋዊ ዕውቅናውን አግኝቶ በወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔውን ለመጥራት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ፣ የጋዜጠኞች መድረክ ምክትል ፕሬዚዳንት በሆኑት አቶ ስለሺ ሐጐስ አማካይነት ተጠቅሷል፡፡

የውይይቱ አጠቃላይ መንፈስ

በውይይቱ ላይ የቀረቡት ሁለት ጽሑፎች የተለያየ መንፈስና ትንታኔ የተከተሉ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጽሑፍ አቅራቢ ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ ሲሆኑ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሬስ አተገባበሩ፣ ተግዳሮቶቹና መፍትሔው›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ የአገሪቱን የሚዲያ ባህል፣ የመንግሥትና የግሉ ሚዲያ ግንኙነት ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ፣ በሙያው ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች የሙያውን መሠረታዊ መርሆዎች አለመከተልና የአገሪቱ አምባገነናዊ ባህል የፈጠረው ጫናና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በመዘርዘር፣ የአገሪቱ ሚዲያ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ለማሳየት የሞከሩበት ነበር፡፡

ሁለተኛው ጽሑፍ አቅራቢ የሕግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ ሲሆኑ፣ ‹‹የፕሬስና የፀረ ሽብር ሕጉ ከፕሬስ ነፃነት አንፃር›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍ ያጠነጠነው ደግሞ በፕሬስና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጆች ላይ ነበር፡፡

በዚህኛው የእሳቸው ጥናት ደግሞ ለመዳሰስ የተሞከሩት የፕሬስ አዋጁ ራሱ ምንድነው? በውስጡ የደነገገው ምንድነው? ለምንድነው የወጣው? የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁስ ከንግግር፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ከተደነገገው ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ አንፃርስ ያለው ትርጓሜስ ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎች ከሕግና ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ከሕገ መንግሥቱና ከፕሬስ አዋጁ አንፃር ለመዳሰስ የሞከሩበት ነው፡፡

በሁለቱም ጽሑፍ አቅራቢዎች በስፋት ከተዳሰሱት ጉዳዮች በተጨማሪ ጋዜጠኞች በኅብረትና በተጠናከረ መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር አለመቻላቸው ተጠቃሽ ነበር፡፡ ዶ/ር አብዲሳ ወጥ የሆነ የማኅበራት ኅብረት አለመኖር ሙያውንና ጋዜጠኞችን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ለማምጣትና መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር እንዳይችሉ እንቅፋት መሆኑን ያወሱ ሲሆን፣ አቶ ተማም በበኩላቸው ጋዜጠኞች ያላቸውን ሚና በመጠቀም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ እንዲሻሻል መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በአመፅ የተወለደ ሚዲያ?

እንደ ዶ/ር አብዲሳ ገለጻ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባህል በአማፅያን የተወለደ እንደሆነ የሚያትት ሲሆን፣ ለዚህም እንደ ማሳያነት ያነሱት ነጥብ ‹‹መጀመሪያ ላይ በጥይት ይታኮሱ የነበሩ ኃይሎች አሁን ግን በየወረቀቱ የፖለቲካ ትግሉን ቀጠሉ፤›› በማለት ነው፡፡

ስለዚህም በድኅረ ኢሕአዴግ የመጣው የመገናኛ ብዙኃን ባህል በአብዛኛው ስለዲሞክራሲና አጠቃላይ ሙያውን የማሳደግ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሳይሆን ይዘግብ የነበረው የፖለቲካ ፅንፈኝነት (Polarization) በማጠንጠን እንደነበር አመልክተዋል፡፡

‹‹ያኛው ወገን [መንግሥት] ጫካ ውስጥ ሲጠቀም እንደነበረው ሚዲያውን ተቆጣጥሮ ሥርዓቱን እየደገፈ እንዲሄድና ቱቦ ሆኖ የመጓዝ ነገር ነው የያዘው፡፡ በዚህኛው በኩል [በሚዲያው] ያለውም ‹‹የት አባህ አንተ›› የሚለውን መንገድ ይዞ ውጥረት (Tension) በሚፈጥር መንገድ ‹‹በሬ ወለደንም›› ጭምር እየጻፈ ሲሄድ የነበረበት ክስተት ነው የተከሰተው፤›› በማለት በመንግሥትና በግሉ ሚዲያ መካከል ጠርዝ ይዞ የመቆምና የመጓዝ ሒደት የአገሪቱን የሚዲያ ጉዞ ምን ያህል እንደጐዳው አብራርተዋል፡፡

የዶ/ር አብዲሳ ጽሑፍ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ያሉትን ዓመታት ከፋፍሎ በፈርጅ በፈርጁ ለማስቀመጥ የሚሞክር ነው፡፡ በተለያዩ ዓመታት ከፋፍለው ባቀረቡት ጽሑፍ ውስጥ በዋነኛነት ሙያው ለአገሪቱ የዲሞክራሲ እሴቶች ማደግና መበልፀግ የሚጠበቅበትን ያህል አስተዋጽኦ አለማበርከቱን ተችተዋል፡፡

በግሉ ፕሬስ መጀመሪያ ዓመታት ላይ ከ260 በላይ ጋዜጦችና መጽሔቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ዶ/ር አብዲሳ፣ ‹‹በመጀመሪያ የጋዜጦችና የመጽሔቶች ማጭድን ማጭድ አለማለታችንና ነገሮችን እየሸፋፈንን መሄዳችንን በሚዲያው ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ እንዳናገኝ አድርጓል፤›› በማለት የሚዲያው ከእውነት መሸሽን እንደ ችግር የቆጠሩ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም መንግሥትም የግል ሚዲያን እንደ አንድ ተፎካካሪ አካል መቁጠሩንና መከታተል መጀመሩን አውስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሚዲያን እንደ አንድ ራሱን የሚችልና በራሱ የሚቆም ጠቃሚ እንደሆነ የማኅበረሰብ ተቋም ቆጥሮ የማሳደግና የመንከባከብ ጉዳይ ከመንግሥትም ሆነ ሙያውን አገለግላለሁ፡፡ ከሚለው አካል እየጠፉ መምጣታቸው ሌላው በመንግሥትና በሙያተኛው መካከል ያለውን ፍጥጫ እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡

በዚህ የተነሳም የብቀላ ጉዳዮች መምጣትና መታየት መጀመራቸውን፣ ከእነዚህ ጋር ተያይዞም መንግሥት ነገሮችን ሁሉ እያጠናከረ ምኅዳሩንም እያጠበበ የመጣበት ክስተት መከሰቱን በጽሑፋቸው ያትታሉ፡፡ ከዚህ ፍጥጫ ጋር በተያያዘም ከ1988 እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ ተፈጥሮ የነበረው የነፃነት ከባቢ እየጠበበ መሄዱን፣ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ ከነበረው የነፃነት ከባቢ እንዴት ወደ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደተሸጋገረ አብራርተዋል፡፡

ይህም ክስተት እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ የደረሰ ሲሆን፣ በ1997 ዓ.ም. ግን ሚዲያው የተለያዩ ነገሮች ከማድረጉም በላይ የዲሞክራሲ ምኅዳሩም ከየትኛውም ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ትልቅ አንድምታ የነበረው እንደ ነበር ገልጸዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው የሕዝቡ የምርጫ ንቃተ ህሊናና የሚዲያው ድርሻ በወቅቱ የተለየ ሥፍራ ተችሮት የነበረ ቢሆንም፣ ዶ/ር አብዲሳ ግን ‹‹በ1997 ዓ.ም. ቢሆን የግሉ ሚዲያ የአገሪቱን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከመደገፍ ይልቅ ከተቃዋሚዎች ጋር የመሠለፍ ጉዳይ ነው የነበረው፤›› በማለት ተችተውታል፡፡ እንደ እሳቸው አተያይ በ1997 ዓ.ም. የግሉ ሚዲያ ነፃ መሆኑን በመተው ለአንድ ወገን ወገንተኝነቱን በማሳየቱ፣ የተለያዩ ክፍሎች ወደ ሥልጣን ለመውጣት እንደ አንድ መንገድ ቆጥረውት ነበር፡፡

ዶ/ር አብዲሳ ከ1999 እስከ 2002 አካባቢ የተወሰነ የማንሰራራት ሁኔታዎች የታየበት ጊዜ እንደ ነበር ቢገልጹም ነገር ግን ድኅረ ምርጫ 97 በወጡ ሕግጋት አማካይነት የተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ይህን ጊዜ በአገሪቱ የሚዲያ ግንባታ ጉዞ ላይ ከፍተኛ ጋሬጣ የበዛበትና ለመሥራት አስቸጋሪ የሆነበት ነው በማለት ይገልጹታል፡፡

ምንም እንኳ ዶ/ሩ የተወሰነ ማንሰራራትና መጠነኛ የሆነ መቻቻል ነበረበት ቢሉም፣ ይህ ግን የመነጨው መንግሥት መቻቻልን ስለፈለገና ስላስቀደመ ሳይሆን ‹‹ጥርስ አብቅሎ የነበረ ሁሉ የወደቀበት›› ወቅት ስለነበረ ነው በማለት ተፈጥሮ የነበረውን የመቻቻል ሁኔታ ይገልጹታል፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የሚዲያ የዕድገት ጉዞን የሚከታተሉ ተቋማትና ግለሰቦች ድኅረ ምርጫ 97 ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩም ሆነ የሚዲያ እንቅስቃሴ ክፉኛ መሽመድመዱን የሚገልጹ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ ዶ/ሩ ከ1999 እስከ 2002 ዓ.ም. ያለው ጊዜ የተወሰነ ያንሰራራበት በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከተቺዎቹ ጋር በሚያስማማ ሁኔታ ደግሞ የፀረ ሽብር አዋጁና የሲቪል ማኅበራት ሕጎች መፅደቅ የነበሩት ብዙ ነገሮች እየተበላሹ እንዲመጡና ተጀምሮ የነበረው የሚዲያ ቁልቁል ጉዞም በከፍተኛ ሁኔታ የታየበት መሆኑን ይስማማሉ፡፡

የፀረ ሽብር አዋጁ የተለጠጠ ትርጓሜ በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦችን ቅድመ ሳንሱር (Self Sensor ship) እንዲያደርጉ እንዳስገደዳቸው ያወሱት ዶ/ር አብዲሳ፣ በፍራቻ የተነሳ የማይነኩ ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡

የግል ማለት ነፃ ማለት አይደለም

በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ የሚታዩ የተለያዩ ዓበይትና አንኳር የሆኑ ተግዳሮቶችን በጽሑፋቸው የዳሰሱት ዶ/ር አብዲሳ፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን የሚዲያ ተግዳሮቶች በሁለት ዋነኛ ክፍሎች ይከፍሏቸዋል፡፡ እነዚህም ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ናቸው፡፡

‹‹ውስጣዊ ችግር በሚባልበት ወቅት ሙያውን በደንብ አድርጐ ተገንዝቦ በአንድ የዲሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ከሚዲያው የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው ብሎ በነፃነትና በራሱ ሳንባ የሚተነፍስ ሚዲያ ያለመኖር ችግር ነው፤›› በማለት ውስጣዊ ችግር የሙያው ባለቤት ራሱ ለሙያው ተገቢውን ክብርና ለሙያው መሠረታዊ እሳቤዎች አለመስጠቱን ይጠቅሳሉ፡፡ እዚህ ላይ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት ጉዳይ የግልና ነፃ ሚዲያ ማለት አንድ ዓይነት ሐሳብ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ‹‹የግል መሆንና ነፃ መሆን አይገናኝም፤›› በማለት አሁን አገሪቱ ውስጥ ያለውን የሚዲያ ባህል የተቹ ሲሆን፤ ‹‹የመንግሥት የሆነ ብቻ አይደለም በመንግሥት ኪስ ውስጥ ያለው፡፡ የግል ሆኖ የተለየያ ዓይነት ግለሰቦች ኪስ ውስጥ የሚገኝ ሚዲያም አለ፤›› ሲሉ የግሉ ሚዲያ ሙያተኞች ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ማክበርና ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ምክር አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ነፃ ማለት ነፃ አስተሳሰብ፣ ነፃ መንፈስ፣ በራስ ሳንባ መተንፈስና ከምንም ጋር ያልሆነና ያመነበትን ነገር ግን ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የሙያውን መሠረታዊ እሴቶች ተጠቅሞ የሚሠራ ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ‹‹ነፃ ነን ስላልን ብቻ ነፃ መሆን እንደማይመጣ›› ሞግተዋል፡፡

ስለዚህ በዋነኝነት በውስጣዊ ችግር የተጠቀሰው ዓብይ ጉዳይ በሙያው የተሰማሩ ግለሰቦች ለሙያው መሠረታዊ እሴቶችና መርሆዎች ተገዥ ለመሆን የመሥራት ችግርን ነው፡፡

በውጫዊ ችግር ከተጠቀሱት መካከል ዋነኛው ደግሞ በአገሪቱ ባህል እየሆነ የመጣው መንግሥትን ጨምሮ በተለያ አካላት ላይ የሚታየው አምባገነናዊ ባህሪ ነው፡፡ ‹‹አጠቃላይ የአገሪቱን ባህል ስንመለከት ለገዳይ የሚዘፈንበት ባህል ነው ያለን፤›› በማለት በአገሪቱ የሰፈነው የጀብደኝነት ባህል በተዘዋዋሪ ሚዲያው ላይ ውጫዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተዋስኦ (Discourse) አለመኖርና እንዲህ ዓይነት ተዋስኦዎች የፈሪዎች ምልክት የሚደረጉበት ጉዳይ መሆኑም ሌላው ችግር ነው ብለዋል፡፡

‹‹ከንግግር ይልቅ ለስድብና ለዘለፋ የተለየ ቦታ አለው›› ባሉት የኢትዮጵያ ባህል መሠረት አንድ ግለሰብ የጀግንነቱ ማሳያ የሚሆነው መሳደብ በመሆኑ ሚዲያውም ከዚህ ዓይነት ከስድብ መንፈስና አዙሪት ውስጥ አለመውጣቱን የውጫዊ ችግር ማሳያ አድርገው አቅርበውታል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት የጀብደኝነት ባህል በአገሪቱም በሙያውም የሚታይ በመሆኑ፣ የመንግሥት ባህሪም የሚመነጨው ከዚሁ ባህል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ምን መደረግ አለበት?

ወደፊት የአገሪቱ የሚዲያ ዕድገት በዋነኛነት ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ ሙያተኞቹ ለሙያው ቅድሚያ መስጠት የሚለው ጉዳይ በጣም አስፈላጊና መሠረታዊ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለሙያው ቅድሚያ መስጠት ማለት ለሙያው መከበር የተደራጁ የተለያዩ ማኅበራት አንድ አቋም በመያዝ በጋራ መሥራት ሲችሉ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የተለያዩ የሚዲያ ማኅበራት ቢኖሩም ሙያው አንድ ጋዜጠኝነት እንደመሆኑ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ውጪ ባሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመሥራት የሚፈለገውን ተፅዕኖ በመንግሥት ላይ መፍጠር እንደሚቻል ተጠቁሞዋል፡፡

የተደራጁ የሙያ ማኅበራት በሌሉበት ወቅት ደግሞ ማንም ሚዲያውን የመጠበቅ ግዴታም ሆነ ኃላፊነት እንደማይኖርበትና በዚህም የተነሳ ሙያው ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ እንደሚሆን ጽሑፍ አቅራቢው በአንድ ጥላ ሥር ሆኖ መንቀሳቀስ ዓይነተኛ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ያሉት የሙያ ማኅበራት እርስ በእርስ በመወነጃጀልና አንዱ አንዱን በመንቀፍ መጠመዳቸውን በመጠቆም፣ ያሉት ማኅበራት በአንድነት እንዲሠሩና የሚዲያ ካውንስል እንዲያቋቁሙ ወትውተዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት የሙያ ማኅበራት በተጠናከረ መንገድ ሲኖሩ ደግሞ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠርና በአገሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፤›› በማለት የገለጹት ዶ/ር አብዲሳ፣ ‹‹ተፅዕኖ መፍጠር ማለት ደግሞ በዚህ አገር ሚዲያው በስፋት እንዲያድግ ማድረግና በሚዲያው ውስጥ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲፈጠሩ ማድረግ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ በአገሪቱ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ አንፃር የተደነገጉ ሕጐች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ሕጐቹንና የሕጐቹን ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያላቸውን ተቃርኖዎችና አፋኝነት በስፋት ከዳሰሱ በኋላ እንደ መፍትሔ ያቀረቡት ሐሳብ ሕጎቹ እንዲሻሩ መጠየቅ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ጋዜጠኞች ያላቸውን ኃይል ሁሉ በመጠቀም በኅብረተሰቡ ዘንድ የሕጎቹን አፋኝነትና ችግሮች በዝርዝር በማቅረብ ሕጎቹ እንዲሻሩ ከፍተኛ ሥራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህ ለግማሽ ቀን የተካሄደው የውይይት መድረክ ምንም እንኳን አዳራሽ ውስጥ የነበሩ ታዳሚዎች በሙሉ ባይመለከቱትም በከበባ ተጀምሮ በከበባ የተጠናቀቀ እንደነበር በማኅበራዊ ድረ ገጾቹ ተዘግቧል፡፡ ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ በዕለቱ በውይይቱ ተሳትፈው የነበሩ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ስም በወረቀት ጽፈው በመያዝ የታሰሩ ጋዜጠኞች ይፈቱ የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s