ከችሎቱ ጀርባ ያለው ጥቁር ዳኛ ማነው? – (በስለሺ ሐጎስ)

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር አስር ቀን 2004 ዓ.ም በእነ ርዕዮት አለሙ ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ በችሎቱ የተሰየሙት ዳኞች በነጻ ህሊና የሰጡት ፍርድ ነው ብሎ ያመነ ሰው አልነበረም፡፡ እዚህም እዚያም ሲወራ የነበረው ውሳኔው በመንግስት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ በርካታ ሰወች ይህንኑ በአደባባይ ጽፈውታል፡፡ ቆየት ብሎ ግን ዳኛው የተጻፈለትን እንዳነበበ የሚገልጹና ተጨማሪ ነገር ለማወቅ የሚገፋፉ መረጃዎች ወደኔ መምጣት ጀመሩ፡፡

እርግጥ የኢትየጵያ የፍትህ ስርአት በተደጋጋሚ ተፈትኖ የወደቀና ነጻነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ አይነት የጥርጣሬ ድምጾች መሰማታቸው በራሱ ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የምር እንዳስብ የሆንኩት ዳኛው የተጻፈለትን እንዳነበበ በመስማቴ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዚያ በፊት በነበረው የፍርድ ሂደት ያስተዋልኳቸው ሦስት አጠራጣሪ ክስተቶቸ ናቸው እንደ ጋዜጠኛም ሆነ እንደ ርዕዮት የቅርብ ሰው ስለ ጉዳዩ ብዙ ለማወቅ እንድታትር የገፋፋኝ፡፡

የመጀመሪያው፣ ርዕዮት በማዕከላዊ ምርመራ ላይ እያለች የታዘብኩት ነው፡፡ ርዕዮት በተያዘች በማግስቱ አራዳ ፍርድ ቤት ቀርባ ፖሊስ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ አባቷና ጠበቃዋ የሆኑት አቶ አለሙ ደግሞ ቤተሰብ እንዲጠይቃትና የህግ ምክር እንድታገኝ አመለከቱ፡፡ ዳኛዋም ፖሊስ ይህንኑ እንዲፈጽም አዘውና የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሰጥተው ችሎቱ አበቃ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ርዕዮት፣ ጠበቃም ሆነ ቤተሰብ ሳታገኝ 28ቱ ቀን አለፈ፡፡

የነበረው አማራጭ የቀጠሮው እለት ጠበቃዋ ገብተው ድጋሜ እንዲያመለክቱ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡ እኛም ፍርድ ቤት ስትመጣ ጠብቀን ቢያንስ አይኗን ለማየት ጓጉተናል፡፡ በዕለቱ የሆነው ግን በጣም አስገራሚም አሳዛኝም ነበር፡፡

ቀጠሮው ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ነበረ፡፡ በዚያን ዕለት ጠዋት 2፡30 ቁርስ ላደርስላት ወደ ማዕከላዊ ስሄድ ከዚያን ዕለት በፊትም ሆነ በኋላ አይቻት የማላውቃት አንዲት ልጅ “ርዕዮትን በሌሊት ወደ ፍርድ ቤት ወስደዋታል ሮጠህ ድረስባት” ብላኝ ካጠገቤ ብን አለች፡፡ ለአቶ አለሙ በስልክ ይህንኑ ነግሬ ወደ ፍርድ ቤቱ አመራሁ፡፡ ቦታው ቅርብ በመሆኑ 10 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ደረስኩ፡፡ እኔ ወደ ግቢው ስገባ ርዕዮት በፒካፕ መኪና ተጭና እየወጣች ነበር፡፡

የፍርድ ቤቱ የቀጠሮ ሰዓት የተለወጠው ባጋጣሚ ወይም በስህተት ሊሆን ይችላል በሚል ይህ ለምን እንደሆነ መዝገብ ቤቱን ጠይቀን የተረዳነው  ኬዙን ያየችው ዳኛ በህመም ምክኒያት ለረጅም ጊዜ ስራ የምትገባው ከሰዓት በኋላ ብቻ መሆኑንና ሁኔታው ለእነሱም እንግዳ ነገር መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም የቀጠሮው ሰዓት ለውጥ በፖሊስ ፍላጎት ሆን ተብሎ ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት በፍርድ ቤቱና በፖሊስ መሀከል ሊኖር የሚገባው መስመር ላይ ችግር አለ ማለት ነው፡፡

ሌላው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለ5 ወራት ያህል ግራና ቀኙን ሲያከራክር ሰንብቶ ታህሳስ 17 2004 ዓ.ም የመጨረሻውን ፍርድ ለመስጠት በተሰየመበት ዕለት የነበረው ሁኔታ እንዲሁ ጥርጣሬውን የሚያጠናክር ነው፡፡ ቀጠሮው ከጠዋቱ 3፡00 የነበረ ቢሆንም በዚያን ዕለት ይሰጣል የተባለውን ፍርድ ለመስማት የተገኙ ሰዎች የችሎቱን አዳራሽ የሞሉት ቀደም ብለው ነበር፡፡ ዳኞቹ 1 ሰዓት አርፍደው 4፡00 ላይ ችሎቱ ተሰየመ፡፡ ወዲያውኑ ውሳኔው ማለቁንና ይሁን እንጂ በኮምፒውተር ተጽፎ ስላላለቀ ከሰዓት በኋላ እናርገው አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነውብሸት ጠበቃ አቶ ደርበው “ከሰዓት ሌላ ቀጠሮ ስላለኝ አልችልም” ብለው ከአራት ቀን በኋላ ለታሀሳስ 21 እንዲሆን አማራጭ አቀረቡ፡፡ ዳኛው ግን አልተቀበሉትም፡፡ “እነዚህ ሰወች ያሉት በማረሚያ ቤት ነው፤ ቀጠሮው ከሚራዘም 7 ሰዓት እንገናኝና እስከ 8፡00 እንጨርሳለን” የሚል አማራጭ አቅረቡና በዚሁ ተስማሙ፡፡

የዳኛው ንግግር የሆነ ጥሩ ነገር ሊኖር ይችላል የሚል ተስፋ ስላጫረብን ሁላችንም ከዚያው ሳንወጣ ሰዓቱ እስኪደርስ መንቆራጠጥ ያዝን፡፡

አይደርስ የለ ሰዓቱ ደርሶ ችሎቱ በሚሰየምበት አዳራሽ ተኮለኮልን፡፡ ዳኞቹ ግን በሰዓቱ የሉም፡፡ ግማሽ ሰዓት አለፈ፤ አልመጡም 8 ሰዓት ሲሆን ሁላችንም ቀጠሮ አለኝ ያሉትን ጠበቃ ደርበውን እያየን መሳቀቅ ያዝን፤  ሰዓቱ እየነጎደ ነው፤ 9 ሰዓት ሆነ፡፡ ዳኞቹም አልመጡም ጠበቃ ደርበውም አልሄዱም፡፡ 9፡45 ላይ ዳኞቹ መጡ፡፡ አቶ ደርበው ግን ቀሩ፡፡

ዳኛው ስለማርፈዳቸው ምንም ሳይሉ አሁንም ጽሁፉ ስላልደረሰ በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት አጀንዳቸውን ማገላበጥ ያዙ፡፡ “አራት ቀን ምን ሲደረግ ይራዘማል” ያሉት ዳኛ ከ23 ቀን በኋላ ለጥር 10 2006ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተው ዕለቱና ችሎቱ አበቃ፡፡ ተስፋችንም እንዲሁ፡፡

ይህ ሁኔታ አንዳች ደስ የማይል ነገር እየተከናወነ እንዳለ የሚናገር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቀደም ሲል ያነሳነውን ጥርጣሬ ወደ እውነት የሚገፋው ተጨማሪ ክስተት፣ ለቀጠሮው መራዘም ምክኒያት ሆኖ የቀረበው ነገር ነው፡፡ የታህሳስ 17ቱ ቀጠሮ ወደ ጥር 10 የተሻገረው ውሳኔው በኮምፒውተር ተጽፎ አለማለቁ ሆኖ ሳለ ዳኛው ጥር 10 ያነበቡት በኮምፒውተር ያልተተየበ የእጅ ጽሁፍ ነበር፡፡ ስለዚህም የቀጠሮ ለውጡ የተካሄደው ከችሎቱ ጀርባ ባለ ሌላ ምክኒያት እንጂ ዳኛው እንዳሉት የኮምፒውተር ጽሁፍ ጉዳይ አይደለም ለማለት ይቻላል፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ትንንሽ የሚመስሉ በርካታ ትዝብቶች ዳኛው የተጻፈለትን እንዳነበበ ከሚገልጸው መረጃ ጋር ተደምረው ሲታዩ የሚሰጡትን ትርጓሜ በማስረጃ ለማረጋገጥ መጠነኛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

ይህን ለማረጋገጥ ሁነኛና ቀላል ዘዴ ሊሆን የሚችለው በእለቱ ዳኛው ያነበበውን የእጅ ጽሁፍና የዳኛውን ትክክለኛ የእጅ ጽሁፍ አግኝቶ ማመሳሰል ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ማስረጃዎች ተገኝተዋል፡፡ ማስረጃዎቹ ዳኛው በዕለቱ ያነበበው ጽሁፍ በራሱ በዳኛው የተጻፈ አለመሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ቀጣዮቹን ሁለት ምስሎች ይመልከቱ

pic 1

pic 2                                                                                                                   መልስ የሚያስፈጋቸው ጥያቄዎች

ጥያቄ 1 የግራ ወይም የቀኝ ዳኛው ሊጽፉት አይችሉም?

    በፍጹም፡፡

ጥያቄ 2 ከፊደል አጣጣሉ በተጨማሪ የፅሁፎቹን ልዩነት የሚያመለክቱ ሌሎች ማስረጃዎች አሉ?

እንዴታ!

ጥያቄ 3 ምናልባት የዳኛው ጽሁፍ የማይነበብ ሆኖ ወይ ደክሞት ወይ በሌላ ምክኒያት ከቅርብ ሰዎቹ አንዱን አጽፎት ቢሆንስ?

እሱም ሊሆን አይችልም፡፡

እኔ የደረስኩበት ድምዳሜ የሚያመለክተው ከዚህ የተለየ ነው፡፡

ከእኔ ድምዳሜ በፊት አንባቢያን እንዲመራመሩበት የሁለት ቀናት ዕድል ልስጥና ከነገ በስቲያ በክፍል ሁለት

  • ጽሁፉ ከዳኞቹ በአንዳቸው ወይም በእነሱ ሰዎች አለመጻፉን የሚያመላክቱ ነጥቦችን
  • በዚህ ጽኁፍ ከጠቀምኳቸው ሁለት ገጽ ማስረጃዎች በተጨማሪ ባለው (የጥፋተኝነት ውሳኔውን ዝርዝር የሚያትና የቅጣት ውሳኔው የተጻፈበት በድምሩ 29 ገጽ የእጅ ጽኁፍ) ላይ ያስተዋልኩትን
  • የጸሀፊውን ማንነት ለመገመት የሚያስችሉ ምልከታዎቼን ጨምሬና እና ሙሉውን ማስረጃ አያይዤ እመለስበታለሁ፡፡

እስከዚያው ከዛሬው ጨለማ ለሚለደው፣ ለነገው በሩህ ቀናችን                                                            ቺርስ!! ብያለሁ፡፡

ስለሺ ሐጎስ – ታህሳስ 14 2006ዓም

ከችሎቱ ጀርባ ያለው ጥቁር ዳኛ ማነው (ክፍል1)pdf

Advertisements

የፀረ-ሽብር አዋጁ ለምን ይሰረዝ? (በስለሺ ሐጎስ )

???????????????????????????????ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአገራችን አገልግሎት ላይ ባለው የፀረ-ሽብር አዋጅ ዙሪያ አንዳንድ የመወያያ ነጥቦችን ለማንሳት ሞክረን ነበር “የፀረ-ሽብር አዋጁ ይሰረዝ ሲባል” በሚል አብይ ርዕስ ለመዳሰስ የተሞከረው የተለያዩ አካላት በፀረ-ሽብር አዋጁ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውን በራሱ መኮነን የዕውነትም የእውቀትም መሰረት የሌለው ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ የጥያቄዎቹን መነሻ ሰበቦች መመርመር ወደ እውነት የሚያደርሰን ብቸኛ መንገድ ነው ተባብለናል፡፡
የዛሬው ቀጠሮአችን የተመሰረተው የፀረ-ሽብር አዋጁን በጥንቃቄ አንድንመረምር በሚያስገድዱን ሶስት ነጥቦች ላይ ነው፡፡ ለመስታወስ እንዲረዳን ሳምንት ያነሳናቸውን እነዚህን ሶስት የመጠየቂያ ነጥቦች አስቀድመን ወደ ዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን እናልፋለን፡፡
ስለ አዋጁ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ስለ እንከን የለሽነቱ የሚሰብኩት መንግስትና ደጋፊዎቹ ብቻ መሆናቸውና የአዋጁን እንከኖች ከመንቀስ ጀምሮ ይሰረዝ እስከሚል ጠንካራ ውግዘት የሚያቀርቡት ደግሞ አሁን ያለውን መንግስት ባንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚቃወሙ አካላት ብቻ ለምን ሆኑ?
አዋጁ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ አስራ ሰባት ጋዜጠኞችና በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና በሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ፖለቲከኞችና የፓርቲ አመራሮች የዚህ አዋጅ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የመንግስት ተቃዋሚዎችና ተቺዎች ከዚህ አዋጅ ኢላማ ውጪ ናቸው ማለት ያስችላልን?
መንግስት፣ በአሸባሪነት ተከሰው ስለታሰሩ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ፖለቲከኞች ሲጠየቅ የሚመልሰው የንጹሀን ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለደህንነታቸው የታሰበላቸው ንጹኃን ዜጎች መንግስት አሸባሪ ያላቸውን እስረኞች እንዲፈታ የታሳሪዎቹን ፎቶ በመያዝ አደባባይ ወጥተው ሲጠይቁ ስለምን ተስተዋሉ?
ከነዚህ የማጠየቂያ ነጥቦች ተነስተን አዋጁን ስንበረብረው የዐዋጁ ዋነኛ ዓለማ ምን እንደሆነና አዋጁ ግንባር ቀደም ኢላማ ያደረገው እነማንን እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት እንችላለን፡፡ የአዋጁን ትክክለኛ አላማና ኢላማውን መለየት ደግሞ ለምን ይሰረዝ? ለምንስ አይሰረዝ? ለሚሉ ጥያቄዎች ልብ የሚሞላ ምክኒያታዊ ምላሽ ለማግኘት ያስችላል፡፡
አላማና ኢላማው
ገዥው ፓርቲ ይህንን አዋጅ ለምን እንዳፈቀረው፣ለምንስ ከሌሎች ህግጋት ሁሉ የበለጠ እንዳሚሳሳለት፣ በእርሱ የመጣ ባይኔ መጣ ያሰኘው ምን እንደሆን ከራሱ አንደበት የተደመጠ ነገር የለም፡፡ ተቃዋሚዎች ግን አዋጁን ለምን እንደጠረጠርኩት ባለፈው ስምንት ኢቲቪ ባሰተላለፈው የፓርቲዎች ክርክር ላይ አፍረጥርጠውታል፡፡ ይኸውም “የአዋጁ አላማ ኢህአዴግን የሚቃወሙና የሚተቹ ዜገችን ስጥ ለጥ እንዲሉ ማድረግ ሲሆን ዋነኛ ኢላማዎቹ ደግሞ እኛ ነን” የሚል ነው፡፡
ይህ ጥርጥሬ ብቻ አይደለም፡፡ ፓርቲዎቹ ለድምዳሚያቸው መነሻ የሆኗቸውን በርካታ ማሳያዎች አቅርበዋል፡፡
የፓርቲዎቹንና የኢሀአዴግን ጉዳይ እዚሁ ጋር እንተወውና ወደ ራሳችን የፍተኝ ነጥቦች እናምራ
አዋጁ ለምን አላማ ወጣ? እነማንን ኢላማ ያደረገ አዋጅ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በአዋጁ የተካተቱን አንቀጾች ቴክኒካዊ የህግ ትርጓሜ አንድምታ በመነሳት መተንበይ ይቻል ይሆናል፡፡ እኔ ግን ይሄን መንገድ አልመረጥኩትም፡፡ ያልመረጥኩት ደግሞ በሌላ ምክኒያት ሳይሆን ስለማላውቅ ነው፡፡ ይልቁንም እኔ በአዋጁ ላይ ያለኝ ዕውቀት የሚነሳው መሬት ላይ ካለው እውነት ነው፡፡ ዐዋጁ የተለጠጠ ትርጓሜ ያላቸውን ድንጋጌዎች መያዝ አለመያዙን አንቀጽ እያጣቀስኩ ቃል እየመነዘርኩ ላስረዳችሁ የሚያስችል ምንም የህግ እውቀት የለኝም፡፡ የእኔ እውቀት “መለስ በቃ” የሚል መፈክርን ፎቶ ማንሳት ብቻ ህገ መንግስቱዊ ድንጋጌዎችን በሃይል ለመናድ፣.በአሸባሪ ድርጅት ውሥጥ በአመራርነትና በውሳኔ ሰጭነት በመሳተፍ፣ ለአሸባሪ ድርጅቶች አባል በመመልመል፣ በማሰልጠንና በማደራጀት ወ.ዘ.ተ በሚሉ ክሶች ወንጅሎ 14 ዓመት ለማስፈረድ የሚያስችል አዋጅ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የሆነው ግን የአዋጁ ድንጋጌዎች ያለቅጥ የተለጠጡ በመሆናቸው ብቻ ነው ለማለት አልችልም፡፡ የከሳሹ ፍላጎት ያለቅጥ በመለጠጡም ጭምር እንጂ፡፡
በዚህ አዋጅ ተከሰው በእስር የሚገኙ ፓለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ስብዕና ቀድም ብሎ የሚያወቅና አደረጉ የተባሉትን ተግባራት የሚያውቅ ሰው “ታዲያ አሸባሪ ያልሆነ ማነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀሬ ነው
ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን እንደ ምሳሌ ማየት ይችላል፡፡ ርዕዮትን በምሳሌነት የማነሳው በደምብ ስለማውቃትና የፍርድ ሂደቷንም በቅርብ የተከታተልኩት ሰለሆነ ብቻ ነው፡፡
ርዕዮት ዛሬ በእስር ላይ የምትገኝ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ሁለት ሰዎች ተጫጩኸው ሲነጋገሩ ቆማ ማድመጥ የማትችል ፍፁም ሰላማዊ ሰው ነበረች፡፡
ቤተሰብ የማስተዳደር ሃላፊነት የተኸከመች ሆና ሳለ ከአነስተኛው የመምህርነት ደሞዟ ላይ ቀንሳ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የሚመጡ ተማሪዎቿን ለመርዳት ወደ መስሪያ ቤቷ በእግሯ ስትመላለስ አውቃለሁ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን መንግስት እንዳበደ ሰው አስሯት ሲያበቃ በአሸባሪነት አስፈርዶ ይኸው ሀገሯ በቃሊቲ ከሆነ ዛሬ 807ኛ ቀኗ ነው፡፡ የመንግስት ባለ ስልጣናት ስለ ርዕዮት አሸባሪነት ሲያወሩ ብቻ ሰይሆን አጠፋች ሰለተለባለው ነገር ማስብ ስጀምር ልቤ ስራ ይፈታብኛል፡፡
የፌድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በርዕዮት ላይ ፍርድ ያልተላለፈ ዕለት ያነበበው የሚከተለውን ነበር፡፡
“በአዲስ አበባ አንዳንድ የአደባባይ ቦታዎች ላይ በቀይ ቀለም “መለስ በቃ” የሚል ዓመፅ የሚያነሳሳ ፅኁፍ ሲፃፍ ቦታው የት እንደሆነ ተከታትላ ፎቶ በማንሳት መረጃ አስተላልፋለች፡፡ ታዛቢዎች ባሉበት ከርሷ ኢሜይል ፕሪንት ተደርጎ የወጣ “ሶሊዳሪቲ ሙቨመንት ፎር ኒው ኢትዮጵያ” የሚል ፅኁፍ የተገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ከህግ ውጪ የሚንቀሳቀሰው ሀይል የሚራምደው አቋም ስለሆነ በመረጃ ማስተላለፍ ላይ ይህ ሲታከልበት ይግባኝ ባይ የፈፀመችው የጋዜጠኝነት ስራ ነው የሚል ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡
የቀረቡ ማስረጃዎች ይገባኝ ባይ የሽብርተኛ ድርጅት አባል ናት ለማለት የሚያስችል ባይሆንም ለሽብርተኛ ድርጅት የሚደርሉ መረጃዎችን በማቀበል በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ የተሳተፈች ስለመሆኑ የሚያሳዩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በሁለተኛው ክስ ላይ የተጠቀሰው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ አዋጅ ቁጥር 652/2002 አንቀጽ 7/1/ በሽብርተኛ ድርጀት ውስጥ በማንኛውም መልኩ የተሳተፈ…. የሚለውም ይህንን የሚያካት ነው፡፡”
ይሄን የፍርድ ቤት ውሳኔ ለቁጥር ለሚታከቱ ጊዜዎች አንብቤዋለሁ፡፡ ርዕዮት የፈፀመቸውን ወንጀል ፈልጌ ማገኘት ግን አልቻልኩም፡፡ ለአመፅ የሚያነሳሳ ወንጀል ሆኖ የቀረበው “መለስ በቃ” የሚለው ፅሁፍ ነው፡፡ ርዕዮት ግን ይህን አልፃፈችም፡፡ ስህተቷ ሆነ የቀረበው “ለሽብርተኛ ድርጅቶች የሚደርሱ መረጃዎችን በማቀበል” የሚለው ነው፡፡ በድረ ገጽ የሚለቀቅን ዜና ለአሸባሪ ድርጅቶች እንዳይደርስ ማድረግ እንዴት እንደሚቻል ግን የሚያወቀው ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ በርዕዮት የተፈፀመ አንዳችም የወንጀል ድርጊት ሳይኖር በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፏን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል፡፡ በየትኛው የሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ? የሚል ጥያቄ ካነሳችሁ ግን መልሱ አይታወቅም፡፡ በአልቃይዳ ውስጥ ይሁን በአልሸባብ ውስጥ አሁንም ከሰይጣን በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለ18 ዓመታት እስር ከዳረጉት ሰበቦች አንዱ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ነው፡፡ የህወሃት አንጋፋ ታጋይና የሀሳብ አባት ተደገርው የሚወሰዱት አቶ ሰብሃት ነጋ የዚሁ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘውትር ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የፀረ-ሽብር ዐዋጅ አቶ ሰብሃትን ገልመጥ እንኳ ለማድረግ ጉልበት አላገኝም፡፡ “ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ የበለጠ እኩል ናቸው፡፡ እንዲል፤ ጆርጅ ኦርዌል፡፡
እነዚህ የፈጠጡ እውነቶች የሚነግሩን የፀረ-ሽብር ዐዋጁ የፀደቀበትን አላማ ቅርጥፍ አድርገው የሚበሉ ተግባራትን በመከወን ላይ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የፀረ-ሽብር አዋጁ ይሰረዝ የምንልበት አንድ አብይ ምክኒያት ይህ አዋጅ አሸባሪነትን በበቂ ሁኔታ መመከት የሚያስችል አቅም የሌለው መሆኑ ነው፡፡
“Trigger factors of terrorism” የተባለ አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ የሽብርተኝነት መቀፍቀፊያ የሆኑ አምስት ምንጮችን አስቀምጧል ከነዚህም አንዱ “የዴሞክራሲ ዕጦት፤ አፈናና የህግ የበላይነት አለመኖር ሀገር በቀል ሽብርተኞች እንዲቀፈቀፉ ያደርጋል፡፡” የሚል ነው፡፡ ይህ አዋጅ ሀሳብን በመቅጣት፣ተቃውሞን በማፈንና ዜጎችን በፍርሃት በመሸበብ የሚፈጥረው ስርዓት ሽብርተኝነትን በማባባስ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል
ማጠቃለያ
በተለያዩ ክፍላተ አለማትና በተለያዩ አዝማናት የተነሱ አምባገነን ነግስታት ዜጎቻቸውን እንደሰም አቅልጠው ለመግዛት ያስቻሏቸው ሁለት መሰሪያዎች አሉ፡፡ አንደኛው ጠብ-መንጃ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ህግ ነው፡፡ በእኛም ሀገር የሆነው ይህ ነው፡፡ የሩቁን ትተን ደርግ፣ ሀገር ምድሩን በክላሽ እየቆላ 17 የግፍ ዓመታትን አስግፎን አልፏል፡፡ አሁን ኢህአዴግ ደግሞ ህግ የክላሽን ቦታ ተክቶ እንዲሰራ በማድረግ አገር ምድሩን በህግ እየቆላው ነው፡፡
ህግ የክላሽን ቦታ ተክቶ በሚሰራባት በዚያች ሀገር፣ ህጋዊነት ይሞታል፡፡ ህጋዊነት በሞተባት በዚያች ሀገር ደግሞ ማንም አይድንም፡፡ ህጋዊነት በሞተባት ሀገር፣ ጋዳፊ እደሆነው መሆን የሁሉም እጣ ፈንታ ይሆናል፡፡ ቀን ሲጥል እንደ ፍየል ታርዶ መጣል እንጂ፣ እንደሙባረክ ፍርድ ቤት የመቆም እድል አይገኝም፡፡ እናም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አንተም ለራሰህ ስትል ሰይፍህን ከፍትህ አንገት ላይ አንሳ፡፡

የጸረ ሽብር አዋጁ ይሰረዝ ሲባል…(በስለሺ ሐጎስ)

???????????????????????????????አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ፓርላማ በ2001 ዓ.ም ያጸደቀው የጸረ ሽብር ህግ (አዋጅ 652) እንዲሰረዝ በይፋ የሚጠይቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ማወጁን ተከትሎ የጸረ ሽብር ህጉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ስር አዲስ መነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን ችሏል፡፡ መንግስት የአንድነትን ጥያቄ ሽብርተኝነትን ከመደገፍ ጋር አያይዞ ያቀረበው ሲሆን የሚሚ ስብሀቱን ክብ ጠረጴዛ ጨምሮ አንዳንድ ሚዲያዎችና ግለሰቦች አንድነት ፓርቲንም ሆነ አዋጁ እንዲሰረዝ የሚጠይቁ ዜጎችን በአሸባሪነት ከመፈረጅ አልፈው መንግስት በዝምታ ሊመለከታቸው አይገባም የሚል የይታፈሱልን ጥሪ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡
እነዚህን ኃይሎች ወደ ፍረጃና ወደ አሳፋሽነት የገፋቸው ዋነኛ ምክኒያት አሁን ያለውን የጸረ ሽብር አዋጅ እንዲሰረዝ መጠየቅ ሽብርን እደግፋለሁ ወይም ጨርሶ የጸረ ሽብር ህግ አያስፈልግም የሚል ትርጓሜ ስለሰጣቸው መሆኑን ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም እነዚህ ሁለት ሰሞነኛ ተቃርኖዎች (የአንድነት ፓርቲ የይሰረዝልን ጥያቄ እና የነ ሚሚ ስብሀቱ ይታፈሱልን ጥሪ) ናቸው፡፡
የጸረ ሽብር ህጉ ይሰረዝ ማለት በርግጥ ሽብርተኞች በሀገራችን ላይ እንዳሻቸው ይፈንጩ ማለት ነውን? አሁን ያለው የጸረ ሽብር አዋጅስ መንግስትና ደጋፊዎቹ እንደሚሉት ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ እንከን የለሽ ህግ ነው? ይህ ጽሑፍ በዋናነት በእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ላይ ያተኮሩ አንዳንድ የመወያያ ሀሳቦችን ለመሰንዘር ይሞክራል፡፡
ሽብር ሲባል…
ሽብርተኝነት ረዥም ዕድሜ ያለው አለም አቀፍ የወንጀል ክስተት ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሁሉም ዘንድ ቅቡል የሆነ አንድ ወጥ ትርጓሜ አላገኘም፡፡ ይሁን እንጂ የሽብርተኝነት ድርጊት አጸያፊና ዘግናኝ ወንጀል በመሆኑ የማይስማማ የለም፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች የሚሆኑት በአብዛኛው ንጹኃን ሰዎች መሆናቸው ሲታሰብ ድርጊቱ ከደረቅ ወንጀልነትም ይዘላል፡፡
ለኛለኢትዮጵያውያን ደግሞ ሽብርተኝነት ከምንም በላይ የከፋ ተግባር ነው፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ሽብርተኝነት ማለት የሰው ልጆች የሚያከብሩት ህግ የሚፈሩት አምላክና የሚጸጽታቸው ህሊና ሲያጡ የሚፈጽሙት የመጨረሻው ሀጢያት ነው፤ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
የራስን አላማ ወይም ፍላጎት ለማሳካት ሲባል የንጹኃንን ህይወት የሚቀጥፍና ህዝባዊ ተቋማትን የሚያወድም ተግባር መፈጸም በምንም አይነት መለኪያ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የሽብርተኝነት ድርጊት በምንም ምክኒያት፣ በየትም ቦታ፣ በማንኛውም ሰው ላይ እንዳይፈጸም አለም ሁሉ የዘመተበት ወንጀል የሆነው፡፡
ጸረ ሽብር ሲባል…
ይህ ወቅት ከመቼውም በላይ አለም አቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻው ተፋፍሞ የቀጠለበት ጊዜ ቢሆንም ዘመቻው ሽብርን ሊያጠፋው ቀርቶ ጋብ ሊያደርገው አለመቻሉ አሳዛኝ እውነት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በመከወን እንዲጠመዱ አስገድዷቸዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከሽብር ስነልቦና ጋር የማይተዋወቅና ሽብርተኝነትን የሚጸየፍ ህዝብ የሚኖርባት ሀገር መሆኗ የጸረ ሽብር ዘመቻውን ከመቀላቀል አላገዳትም፡፡ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለሽብርተኞች የተጋለጠ መሆኑና አሜሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ላወጀችው የጸረ ሽብር ዘመቻ የቀጠናው ግምባር ቀደም አጋር በመሆኗ የዘመቻው ንቁ ተሳታፊ ከሆኑ ሀገራት ምድብ ተቀላቅላለች፡፡ ከአራት አመት በፊትም ለብዙ ትችቶች የተጋለጠውን አወዛጋቢ የጸረ ሽብር ህግ (አዋጅ 652) አጽድቃ ተግባር ላይ አውላለች፡፡
ሽብር አጸያፊና ዘግናኝ የወንጀል ድርጊት እንደመሆኑ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማጥፋት የሚደረጉ አለም አቀፍም ይሁን ሀገር አቀፍ ትግሎችን ሽብርን የሚኮንኑ አካላት ሁሉ ሊደግፉና ሊተባበሩ የሚገባ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስከዛሬ ከተደረጉና አሁንም እየተደረጉ ካሉ የጸረ ሽብር ዘመቻዎችም ሆነ በአለምአቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ ጸድቀው ተግባር ላይ ከዋሉ ህጎች መሀከል አብዛኞቹ፣ በተለያዩ አካላት የመረረ ተቃውሞና ትችት ተነስቶባቸዋል፡፡ በዘመቻው ግምባር ቀደም የሆኑ ሀገራትን ሳይቀር ለውዝግብ የዳረጉ የጸረ ሽብር ህጎችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡
ምስራቅ አፍሪካን ከሽብርተኞች ለማጽዳት አሜሪካና ኢትዮጵያ በአጋርነት እየሰሩ ያሉ ወዳጅ ሀገራት ሆነው ሳለ የኢትዮጵያን የጸረ ሽብር ህግ በጥብቅ ከሚተቹ ሀገራት መሀከል አንዷ አሜሪካ ናት፡፡ ህጉን ከመተቸትም ባለፈ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ኢትዮጵያ አሸባሪ ብላ ያሰረቻቸውን ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንድትፈታ መጠየቁ በጸረ ሽብር ተግባራት ላይ ያለው ውዝግብ ዛሬም ድረስ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው፡፡
የተቃውሞዎቹና የውዝግቦቹ ዋነኛ መነሻ፣ ሽብር ማለት ምን ማለት ነው? የሽብርተኝነት ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው? አሸባሪስ ማነው? በሚሉ አበይት ጥያቄዎች ላይ የጸረሽብር ዘመቻው ተዋናዮች ስምምነት ላይ ሊደርሱ ያለመቻላቸው ነው፡፡ እነዚህን አበይት ጥያቄዎች በመበየን ሂደት ላይ ሽብርተኝነትን ከሰላማዊ የፖለቲካ ተቃውሞዎች፣ ከጸረ ጭቆና እንቅስቃሴዎችና በህግ ዕውቅና ካገኙ ሰብአዊ መብቶች ጋር የሚያጣርሱ በርካታ መንግስታት በመኖራቸው ውዝግቡ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡
የጸረ ሽብር አዋጁ ይሰረዝ ሲባል…
የኢትዮጵያ ፓርላማ ካጸደቃቸው አዋጆች መሀከል የጸረ ሽብር አዋጅ በመባል የሚጠራው አዋጅ 652 አንዱ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ከረቂቅነቱ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በርካታ ውግዘቶችና ተቃውሞዎችን እያስተናገደ አመታትን ዘልቋል፡፡ የአዋጁ አንቀጾች ቴክኒካዊ የህግ ትርጓሜ ያለቅጥ መለጠጥ ብቻ ሳይሆን አዋጁ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ያለው አተገባበር ለክፉ ተቃውሞ ዳርጎታል፡፡ አዋጁ ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያገኙ መብቶችን ይጋፋል ብቻ ሳይሆን መንግስት ተቃዋሚዎቹንና ተቺዎቹን ለማጥቃት እንደ መሳሪያ እየተጠቀመበት እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
እንዲህ አይነት ተቃውሞዎች ሲነሱ መንግስት በአዋጁ ላይ ተግባራዊ ማሻሻሎችን ለማድረግ በሚያስችል ሆደ ሰፊነት ወደ መግባባት የሚያመጡ ውይይቶችን ማካሄድ፣ ሽብርን የመከላከል አንዱ አካል እንደሆነ ማመን ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ማጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ የጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ተቃውሞ ያስነሱትንና አዋጁ እንዲሰረዝ ለመጠየቅ ህጋዊና ሰላማዊ የህዝብ ንቅናቄ ውስጥ የተሳተፉትን አካላት በአሸባሪነት ለመፈረጅ ሲዳዳው ተመልክተናል፡፡ ይህ አይነቱ የመንግስት አተያይ አዋጁ ያስከትላል ተብሎ ከሚሰጋው የከፋ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ ባህሪ ነው፡፡
በአለም ላይ የተከሰቱ ሁነቶች የሚያሳዩን ሀቅ ጥቂት የማይባሉ አምባገነን መንግስታት በጸረ ሽብር ዘመቻ ስም በሚገዙት ህዝብ ላይ ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ነው፡፡ አንዳንዶቹም በሽብር ጥቃት ሊደርስ ከሚችለው አደጋ የከፉ ወንጀሎች ናቸው፡፡ የሊቢያ መሪ የነበረው ሟቹ መሀመድ ጋዳፊ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበትን የሀገሩ ዜጎች ሲጨፈጭፍ አሸባሪ ናቸው በሚል ሰበብ ነበር፡፡
ተቃውሞ የሚያነሱባቸውን የነጻነት ታጋዮች በአሸባሪነት ፈርጀው የሚያሳድዱ፣ የሚገሉና የሚያስሩ መንግስታት መታየታቸው የጸረ ሽብር ዘመቻ የተባለ ሁሉ የጸረ ሽብር ዘመቻ አለመሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ዛሬ አለም ሁሉ የነጻነትና የሰላም ተምሳሌት አድርጎ የሚያያቸው ማህተመ ጋንዲና ኔልሰን ማንዴላ ያኔ በሚታገሏቸው ገዢዎች በአሸባሪነት መፈረጃቸው ደግሞ አሸባሪ የተባለ ሁሉ አሸባሪ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡
በመሆኑም ማናቸውም የጸረ ሽብር ህጎች ሲጸድቁም ሆነ ተግባር ላይ ሲውሉ ለታሰበላቸው ሽብርን የመከላከል አላማ ብቻ እንዲውሉ መወትወትና ከአላማቸው በተቃራኒ ላለ ተግባር ሲያገለግሉ መቃወም ሽብርን ከመደገፍ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም የጸረ ሽብር ህግ ከጸደቀበት አላማ በተቃራኒ ሲውል ከሽብር ጥቃቶች የማይተናነስ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ተቃውሞው ሽብርን የመከላከል አንዱ አካል ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አንጻር አንድነት ፓርቲ የጸረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ያነሳውን ጥያቄ ለመደገፍም ሆነ ለማውገዝ የጥያቄውን መነሻ ሰበቦች መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ድጋፉና ውግዘቱም መሆን ያለበት በጥያቄው መነሻ ሰበቦች ላይ ብቻ እንጂ አዋጁ ይሰረዝ የሚል ጥያቄ መነሳቱን በራሱ እንደ ስህተት ማየትና አሸባሪነትን ከመደገፍ ጋር ማያያዝ ከምክኒያትም ከዕውቀትም ጋር የተጣላ አካሄድ ይሆናል፡፡
እንከን-የለሽ አዋጅ ሲባል
መንግስት ስለዚህ አወዛጋቢ አዋጅ እንከን የለሽነት ብዙ ጊዜ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ህጉ የዳበረ የዴሞክራሲ ልምድ ካላቸው ሀገራት መቀዳቱን በመግለጽ አዋጁ ምንም የማይወጣለት መሆኑን በተደጋጋሚ ሰብኳል፡፡ በአዋጁ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ትችቶችን ከማጣጣልም ቦዝኖ አያውቅም፡፡
ይህ የመንግስት አተያይ እንዳለ ሆኖ በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ ድንጋጌዎች አሉ ለማለት ወይም ስለ አዋጁ እንከን የለሽነት ለመመስከር የሰከነ የህግ ትንታኔ ያስፈልጋል፡፡ አዋጁ ይሰረዝ የሚለውን ጥያቄ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወምም እንዲሁ በአዋጁ ላይ የሚነሱትን ክርክሮች መፈተሸ ተገቢ ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከትንታኔውና ከፍተሻው በፊት አዋጁን ለከፋ ጥርጣሬ የሚዳርጉ ሦስት ገፊ ምክኒያቶች አሉ፡፡
1ኛ የጸረ ሽብር አዋጁ ላይ የሰፈረው የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር እንደሚገልጸው ህጉ ሊወጣ የቻለው “ሕዝቦች በሰላም በነጻነትና በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር ያላቸው መብት ከሽብርተኝነት አደጋ ሁልጊዜ መጠበቅ ያለበት በመሆኑ” በማለት የአዋጁን አላማ ህዝባዊነት ያስረዳል፡፡
በርግጥ ይህ አዋጅ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የወጣ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ፍተሻ ከመጀመራችን በፊት ስለ አዋጁ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ስለ እንከን የለሽነቱ የሚሰብኩት መንግስትና ደጋፊዎቹ ብቻ መሆናቸውና የአዋጁን እንከኖች ከመንቀስ ጀምሮ ይሰረዝ እስከሚል ጠንካራ ውግዘት የሚያቀርቡት ደግሞ አሁን ያለውን መንግስት ባንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚቃወሙ አካላት መሆናቸው ብቻ በአዋጁ አላማ ላይ አንዳች ጥያቄ ለማንሳት የሚጋብዝ ነው፡፡
2ኛ አዋጁ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ አስራ ሰባት ጋዜጠኞችና በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና በሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ፖለቲከኞችና የፓርቲ አመራሮች የዚህ አዋጅ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የመንግስት ተቃዋሚዎችና ተቺዎች ከዚህ አዋጅ ኢላማ ውጪ ስለመሆናቸውና አዋጁ ኢላማ ያደረገው በርግጥ አሸባሪዎችን ብቻ ስለመሆኑ እንድንመረምር ይገፋፋል፡፡
3ኛ መንግስት፣ በአሸባሪነት ተከሰው ስለታሰሩ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ፖለቲከኞች ሲጠየቅ የሚመልሰው የንጹሀን ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለደህንነታቸው የታሰበላቸው ንጹኃን ዜጎች መንግስት አሸባሪ ያላቸውን እስረኞች እንዲፈታ የታሳሪዎቹን ፎቶ በመያዝ አደባባይ ወጥተው ሲጠይቁ ተስተውሏል፡፡ ይህ ወለፈንዳዊ ሁነት አመዛዛኝ ህሊና ያለውን ማንንም ሰው፣ አሸባሪ ተብለው የታሰሩት ሰዎች በርግጥ አሸባሪ ናቸው? ከሚል ጥያቄ አያስመልጥም፡፡
እነዚህ ሦስት ነጥቦች የጸረ ሽብር አዋጁን እንከን የለሽነት እንድናምን ሳይሆን አዋጁ በጥንቃቄ መፈተሸ እንዳለበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመሆኑም አንድነት ፓርቲ ይሰረዝ ያለበትን ምክኒያት በዝርዝር የማስረዳት ሀላፊነቱን ለራሱ ለአንድነት በመተው እኛ ግን በሚቀጥለው ሳምንት “የጸረ ሽብር አዋጁ ለምን ይሰረዝ?” የሚል አብይ ጥያቄ በማንሳት ፍተሻችንን እንጀምራለን፡፡
የሳምንት ሰው ይበለን
ቺርስ!!